በቅርቡ ስለሚመሰረተው ነፃ የንግድ ቀጠና ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ አመራሮች ገለጻ ተደረገ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ በድሬዳዋ በሚቋቋመው ነፃ የንግድ ቀጠና ዙሪያ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው እና የሥራ ባልደረቦቻቸው ገለፃ አድርገዋል፡፡
ነጻ የንግድ ቀጠናው በሀገር ደረጃ ያለውን አስፈላጊነት በተመለከተ የተለያዩ የመንግስት ተቋማትን ያካተተ የጥናት ቡድን በማቋቋም ቅድመ አዋጭነት ዳሰሳ ጥናት መደረጉን በገለጻቸው ጠቁመው÷ በኢትዮጵያ ነፃ የንግድ ቀጠና መመስረት አዋጪና አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ነጻ የንግድ ቀጣና የመጀመሪያ ትግበራውን በድሬዳዋ ከተማ መመስረት አዋጭ እንደሆነ የገለጹት ሚኒስትሯ÷ ትኩረት የተደረገባቸው ዘርፎችም አጠቃላይ ንግድ፣ ሁሉን አቀፍ የሎጅስቲክስ አገልግሎትና የአምራች ዘርፉ (የኤክስፖርት ማቀነባበርና ኤክስፖርት ማድረግ) መሆኑን አመላክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በካርጎ፣ በሎጂስቲክስና በሥራ አመራር በረጅም ዘመን ያካበተውን ልምድ በመጠቀም÷ በነፃ የንግድ ቀጠና ምስረታ ውስጥ የራሱን ሚና ሊጫወት እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው÷ የሀገራትን ተሞክሮ መሠረት በማድረግ አሁን በድሬዳዋ እውን ለመሆን የተዘጋጀውን ነፃ የንግድ ቀጠና ማጠናከርና ማስፋት ይገባል ማለታቸውን የሚኒሰስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
ለዚህም በነፃ የንግድ ቀጠናው ምስረታ ላይ አየር መንገዱ የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት አረጋግጠዋል፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!