Fana: At a Speed of Life!

የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት 2ኛ ዓመት የምስረታ በዓል እየተከበረ ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምሥረታ 2ኛ ዓመት በዓል በሐዋሳ ከተማ ሲዳማ ባሕል አዳራሽ እየተከበረ ነው።
በመርሐ ግብሩ የክልሉ ዋና አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ፣ የክልሉ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ÷ የክልሉን ምስረታ በዓል ስናከብር የህዝቡን ጥያቄ ለማስመለስ ለ130 ዓመታት የታገሉትን ሰማዕታት እያሰብን ነው ብለዋል።

ለዘመናት በተደረገው ዕልህ አስጨራሽ ትግል ሕዝቡ ራሱን በራሱ ለማስተዳደር ችሏል ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ።

ባለፉት ሁለት ዓመታት የክልልነት ጥያቄዎች ምላሽ የሚሆኑ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ስራዎች መከናወናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የህዝቡን የልማት ጥያቄዎች ሁሉ በአንድ ጊዜ መመለስ ባይቻልም በመንገድ መሠረተ ልማት፣ በድልድይ ሥራ፣ በንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ በከተማ ልማት፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በቱሪዝምና በመሳሰሉት የልማት ዘርፎች ላይ የክልሉን ልማት ከፍ ያደረጉ ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀዋል።

በመንገድ መሰረተ ልማት ዝርጋታ የክልሉን ህዝብ የዘመናት ጥያቄ መመለስ መቻሉን ጠቁመው÷ ከዚህ በበለጠ መሰረተ ልማቱን ለማስፋፋት በትኩረት እንደሚሰራም አመላክተዋል።

የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ሽፋን ለማሳደግ በተሰሩ ስራዎች ከሁለት ዓመት በፊት 37 በመቶ የነበረውን የውሃ አቅርቦት ወደ 51 በመቶ ማሳደግ መቻሉም ተመላክቷል።

ክልሉ አሁን ካለበት የኢኮኖሚ ደረጃ ከፍ እንዲል በ10 ዓመቱ ዕቅድ መሰረት በሁሉም የልማት ዘርፎች ለውጥ ለማምጣት በልዩ ትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

ክልላችንንም ሆነ ኢትዮጵያን የዕድገት ማማ ላይ ለማድረስ የውስጥ አንድነታችንን አጠናክረን ሰላማችንን ጠብቀን እንቀጥላለንም ነው ያሉት።

 

በቢቂላ ቱፋ እና ታመነ አረጋ
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.