የሀገር ውስጥ ዜና

የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት 2ኛ ዓመት የምስረታ በዓል እየተከበረ ነው

By Melaku Gedif

July 04, 2022

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ÷ የክልሉን ምስረታ በዓል ስናከብር የህዝቡን ጥያቄ ለማስመለስ ለ130 ዓመታት የታገሉትን ሰማዕታት እያሰብን ነው ብለዋል።

ለዘመናት በተደረገው ዕልህ አስጨራሽ ትግል ሕዝቡ ራሱን በራሱ ለማስተዳደር ችሏል ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ።

ባለፉት ሁለት ዓመታት የክልልነት ጥያቄዎች ምላሽ የሚሆኑ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ስራዎች መከናወናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የህዝቡን የልማት ጥያቄዎች ሁሉ በአንድ ጊዜ መመለስ ባይቻልም በመንገድ መሠረተ ልማት፣ በድልድይ ሥራ፣ በንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ በከተማ ልማት፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በቱሪዝምና በመሳሰሉት የልማት ዘርፎች ላይ የክልሉን ልማት ከፍ ያደረጉ ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀዋል።

በመንገድ መሰረተ ልማት ዝርጋታ የክልሉን ህዝብ የዘመናት ጥያቄ መመለስ መቻሉን ጠቁመው÷ ከዚህ በበለጠ መሰረተ ልማቱን ለማስፋፋት በትኩረት እንደሚሰራም አመላክተዋል።

የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ሽፋን ለማሳደግ በተሰሩ ስራዎች ከሁለት ዓመት በፊት 37 በመቶ የነበረውን የውሃ አቅርቦት ወደ 51 በመቶ ማሳደግ መቻሉም ተመላክቷል።

ክልሉ አሁን ካለበት የኢኮኖሚ ደረጃ ከፍ እንዲል በ10 ዓመቱ ዕቅድ መሰረት በሁሉም የልማት ዘርፎች ለውጥ ለማምጣት በልዩ ትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

ክልላችንንም ሆነ ኢትዮጵያን የዕድገት ማማ ላይ ለማድረስ የውስጥ አንድነታችንን አጠናክረን ሰላማችንን ጠብቀን እንቀጥላለንም ነው ያሉት።