“ሞት ካልቀደመኝ እስከ ዩኒቨርስቲ ቀጥዬ መማር እፈልጋለሁ” የሚሉት የ53 ዓመቱ የ8ኛ ክፍል ተፈታኝ አባ ዘውገ በቀለ
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 28 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የ53 ዓመቱ የዕድሜ ባለፀጋ አባ ዘውገ በቀለ ሙላቴ የ2014 የ8ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተና እየወሰዱ ነው፡፡
አባ ዘውገ፥ ፈተናውን እየወሰዱ የሚገኘው በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 አስተዳደር በቃሊቲ ቅድመ መደበኛና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው፡፡
አባ ዘውገ ትምህርታቸውን በማታዉ የትምህርት ክፍለ ጊዜ ሲከታተሉ መቆየታቸውም ነው የተመላከተው፡፡
እኚህ አባት ሁሉም ሰው በዕድሜና በመሰል ጉዳዮች ሳይረታ ባገኘው አጋጣሚ መማር አለበት፤ እኔም ሞት ካልቀደመኝ እና ፈጣሪ ከረዳኝ እስከ ዩኒቨርሲቲ በመቀጠል በማገኘዉ ዕዉቀት ህዝቤን አገለግላለሁ ፈጣሪ ሀገራችንን እና ህዝቦቿን ይባርክ ብለዋል።
የወረዳው ትምህርት ጽኅፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢፋ አብሼ በበኩላቸው፥ “ትምህርት ዕድሜን አይገድብም ፤ ሁሉም ሰው ለመማር አዕምሮውን ዝግጁ ካደረገ የሚገድበው ነገር እንደሌለ እኚህ አባት ለዘመኑ ትዉልድ ትልቅ ማስተማሪያ ናቸው” ብለዋል፡፡
ትምህርት ተቀጥሮ ለመስራት ብቻ ሳይሆን ለኅሊና እርካታ ጭምር መሆኑንም የአባ ዘውገ ታሪክ ትልቅ ማስተማሪያ መሆኑን ነው ኃላፊው ያነሱት፡፡
የወረዳው ትምህርት ጽኅፈት ቤት ኃላፊው ለአባ ዘውገ መልካም የፈተና ጊዜ እና ጥሩ ውጤትም መመኘታቸውን ከአዲስ አበባ ከንቲባ ጽኅፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡