Fana: At a Speed of Life!

በኮንትሮባንድ የገቡ ሁለት ኮንቴነር ልባሽ ጨርቅ እና ጫማዎችን ተያዙ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ፖሊስ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመቀናጀት ባደረጉት ክትትል በኮንትሮባንድ የገቡ ሁለት ኮንቴነር ልባሽ ጨርቅ እና ጫማዎችን መያዙን አስታወቀ፡፡
 
በህገ ወጥ መንገድ ወደ አዲስ አበባ ከተማ የገቡት ሁለት ኮንቴነር ልባሽ ጨርቅ እና ጫማዎች የተያዙት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አጠና ተራ እና አዲሱ ሰፈር ተብለው በሚጠሩት አካባቢዎች ነው፡፡
 
አዲስ አበባ ፖሊስ እንዳስታወቀው ተሽከርካሪዎቹ ኮንቴነሮቹን ጭነው ጨለማን ተገን በማድረግ ሲንቀሳቀሱ ሰኔ 28 ቀን 2014 ዓ.ም ከሌሊቱ 8 ሰዓት ገደማ የአዲስ አበባ ፖሊስ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመቀናጀት ባደረጉት ክትትል ተይዘዋል፡፡
 
በህገ-ወጥ መንገድ ወደ አዲስ አበባ የገቡትን እና በቁጥጥር ስር የዋሉትን ዕቃዎች ለቃሊቲ ጉምሩክ የማስረከብ ስራ መሰራቱንም ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
ጨለማን ተገን በማድረግ እና የሰዎች እንቅስቃሴ ጭር የሚልበትን አጋጣሚ በመጠበቅ ተመሳሳይ ወንጀል የሚፈፅሙ ግለሰቦች ከፀጥታ አካላት ክትትል እና ከህብረተሰቡ እይታ እንደማያመልጡ ተገንዝበው፤ ከድርጊታቸው ሊታቀቡ እንደሚገባ ፖለስ አሳስቧል፡፡
 
በከተማው ውስጥ የሚፈፀሙ ህገ-ወጥ ተግባራትን ለፀጥታ አካላት በመጠቆም ህብረተሰቡ እያደረገ ያለውን ተባባሪነት አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ ቀርቧል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.