Fana: At a Speed of Life!

የንጹሃንን ደም በከንቱ የሚያፈስሱ የትኞቹም አሸባሪ ኃይላት በጀመርነው መንገድ ጉዟችንን አጠናክረን ከቀጠልን ይጠፋሉ – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

 

የንጹሃንን ደም በከንቱ የሚያፈስሱ የትኞቹም አሸባሪ ኃይላት በጀመርነው መንገድ ጉዟችንን አጠናክረን ከቀጠልን ይጠፋሉ – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 30 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአገራችን የንጹሃንን ደም በከንቱ የሚያፈስሱ የአሸባሪው ሸኔም ሆነ ሌሎች አሸባሪ ኃይላት በጀመርነው መንገድ ጉዟችንን አጠናክረን የምንቀጥል ከሆነ ይጠፋሉ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስት ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች 6ኛ ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 16ኛ መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ተካሂዷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስብሰባው የምክር ቤቱ አባላት ወቅታዊና አገራዊ ጉዳዮች ላይ ላቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም በቅርቡ በግፍ ሕይወታቸውን ላጡ እና ለተገደሉ ንጹሃን ዜጎች የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልጸዋል፡፡

ባልሰሩት ወንጀልና በማያውቁት ጉዳይ ኑሯቸውን ለማሸነፍ ደፋ ቀና በሚሉ ንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመው ግድያ የሚያሳዝን እና የሚወገዝ ነው ሲሉም በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡

ሕይወታቸውን ባለመታደጋችን እንደ ሀገርና እንደ መንግስት ጥልቅ ሀዘን ይሰማናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ እነዚህ ኃይሎች ዓላማና ግብ የሌላቸው፣እሳቤያቸውም ጥፋት ስለሆነ የእኛን ጉዞ ማደናቀፍ አይችሉም ብለዋል፡፡

አክለውም እነዚህ ኃይሎች ኢትዮጵያውያንን መግደልና መፈተን ይችሉ እንደሆን እንጂ ከዋነኛው ዓላማችን ሊያስቀሩን አይችሉም ነው ያሉት፡፡

ግድያው የሚፈጸማመው አንዳንዶች እንደሚሉት መንግስት በቸልታ ጉዳዩን አይቶት ሳይሆን፥ መንግስት የዜጎችን ሕይወት ለመታደግ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የሚፈጠረውን ችግር ለማስቀረት ጥረት ሲያደርጉ ሕይወታቸውን የሚገብሩ የጸጥታ ኃይሎችና ሌሎች አመራሮች መኖራቸውንም ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ በተለያዩ አካባቢዎች ሕይወታቸውን ያጡ የጸጥታ አካላት ለሚከፍሉት መስዋዕትነትም ዕውቅና መስጠትና ምስጋና ማቅረብ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የሽብር ድርጊት አሁን ላይ በአደጉ አገሮች ጭምር የሁለም ዓለም ፈተና መሆኑን ገልጸው፥ ሽብርተኝነት የኢትዮጰያ ብቻ ፈተና አይደለም ብለዋል።

ስለሆነም ሁኔታው ውስብስብ ስለሆነ እንዴት መከላከል ይቻላል በሚለው ላይ በቂ መረጃ ማግኘት፣ መረዳትና ችግሩን ለመከላከል የራስን ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ነው የጠቆሙት፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.