የሀገር ውስጥ ዜና

የቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል ከደረሰበት ችግር ፈጥኖ በማገገም የተሟላ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ይደነቃል- የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ

By Shambel Mihret

July 07, 2022

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል ከደረሰበት ችግር ፈጥኖ በማገገም ለተገልጋዮች የተሟላ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ አደነቁ፡፡

ዶክተር አየለ ተሾመ የቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታልን በጎበኙበት ወቅት÷ ሆስፒታሉ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ካደረሰበት ጉዳት ፈጥኖ አገግሞ ለተገልጋዮች የተሟላ አገልግሎት መስጠቱ መጀመሩ የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡

በቀጣይም ጤና ሚኒስቴር የጎደሉ የህክምና መሳሪያዎችን እንደሚያሟላ እና ሆስፒታሉ የሚጠናከርበትን ሁኔታዎች ያመቻቻል ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

የቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ ተበጀ በበኩላቸው÷ ከታህሳስ 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለድንገተኛ፣ ለወሊድና ለተመላላሽ ቋሚ ታካሚዎች አገልግሎት መስጠት መጀመሩን እና አገልግሎቱንም እያሻሻለ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

የተለያዩ ተቋማት፣ ባለሀብቶችና ግለሰቦች ባደረጉት ድጋፍ ሆስፒታሉ የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጥ ማስቻሉን ጠቁመው÷ በቀጣይም የጎደሉትን አሟልቶ ወደ ነበረበት አሰራር እንዲመለስ የሁሉም ድጋፍና ክትትል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!