Fana: At a Speed of Life!

ሠራዊቱ በልማት ስራዎች ላይ የሚያሳየው ተሳትፎ ለሀገርና ለሕዝብ ያለውን ፍቅርና ክብር የሚያሳይ ነው – አቶ ርስቱ ይርዳ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የመከላከያ ሠራዊት የሀገርን ሉዓላዊነት ከማስጠበቅ በተጓዳኝ በልማት ሥራዎች በንቃት በመሳተፍ እያከናወነ ያለው ተግባር ለሀገርና ለሕዝብ ያለውን ክብርና ፍቅር የሚያሳይ መሆኑን የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳ ተናገሩ።
የደቡብ ክልልና የወላይታ ዞን ከፍተኛ አመራሮች በብላቴ የኮማንዶና አየር ወለድ ኃይል ማሰልጠኛ ማዕከል ዛሬ የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ አከናውነዋል።
በችግኝ ተከላ ሥነ ሥርዓቱ ላይ አቶ ርስቱ ይርዳ እንደገለጹት÷ መከላከያ ሠራዊት ለሀገር ሉዓላዊነትና ለህዝብ ሰላም ሲል እየከፈለ ካለው አብይ ተልዕኮ በተጓዳኝ በልማት ስራዎች በመሳተፍ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ የጎላ ነው።
መከላከያ ሠራዊቱ የሀገር ሰላምና ሉዓላዊነት የማስከበር ስራዎቹ ባለፈ በውጪ በሚሰማራባቸው የሰላም ማስከበር ስራዎች ሀገርን ያኮራ አመርቂ ተግባራት እያከናወነ እንደሚገኝም መናገራቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመላክታል።
በተለያዩ የልማት ስራዎች በንቃት በመሳተፍ አቅመ ደካሞችን የማገዝና የመደገፍ ተግባራቱ በሀገር ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ከሀገር ውጭም በችግኝ ተከላ በግብርና ስራዎችና ሌሎች ተግበራት አኩሪ ተግባር ማከናወኑን ገልጸዋል።
”በህይወታቸው፣ በደማቸውና በጉልበታቸው እያከናወኑ ያሉት የሀገራቸው ባንዲራ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ የማድረግ ስራ ያኮራናል” ብለዋል።
በችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ የመከላከያ ሠራዊቱ ብቻ ሳይሆን በማዕከሉ የደቡብ ክልል ፖሊስና የፌዴራል ፖሊስ ልዩ ኮማንዶ ሰልጣኞች በጋራ መሳተፋቸው እንዳስደሰታቸውም አቶ ርስቱ ጠቁመዋል።
ማሰልጠኛ ማዕከሉ ከዋና ተግባሩ በተጓዳኝ የክልሉን ልዩ ሃይል በማሰልጠን እያደረገ ላለው ተግባርም ምስጋና አቅርበዋል።
የብላቴ የኮማንዶና አየር ወለድ ኃይል ማሰልጠኛ አዛዥ ኮሎኔል ቦጃ አጋ በበኩላቸው÷ መከላከያ ሠራዊቱ ጸረ ህዝብ ሃይሎች እያደረጉት ያለውን አፍራሽ ተግባር ለመመከት እየከፈለ ካለው የህይወት መስዋዕትነት ባለፈ ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርግ ስራ ላይ እየተሳተፈ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
”ህዝብ በሚሰራው ስራ ላይ በመሳተፍና ነገ ውጤቱን ስናይ በጣም ደስ ያሰኛል” ያሉት ኮሎኔል ቦጃ÷ ከዚህ በተጓዳኝ በአካባቢው ያሉ ባለሀብቶችንና ነዋሪውን ህዝብ በማገዝና ሰላም በማስከበር ስራ ላይም በንቃት እየተሳተፉ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል÷ አቶ ርስቱ ይርዳ በወላይታ ዞን በግል ባለሀብት እየለማ ያለ የበቆሎ ምርጥ ዘር ብዜት ጎብኝተዋል፡፡
በዚሁ ወቅት እንደገለጹት÷ ምርታማነትን ለማሳደግ የተጀመረውን ጥረት ውጤታማ ለማድረግ የምርጥ ዘር የዘር ብዜት ማዕከላትን ማስፋፋት ይገባል።
በክልሉ ከ200ሺ ሄክታር በላይ መሬት በበቆሎ ሰብል ይሸፈናል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ ይህንን ተከትሎም የምርጥ ዘር ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን አብራርተዋል።
በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የምርጥ ዘር ብዜት ማስፋፋት የተጀመረውን የምርታማነት ጉዞ እውን እንደሚያደርገውም ርዕሰ መስተዳድሩ አስረድተዋል።
በክልሉ ያሉትን ጸጋዎች በመጠቀም ምርታማነትን መጨመር የሚያስችሉ ስራዎችን ማከናወን ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ አጽንኦት ሰጥተዋ፡፡
ባለሃብቱ በ790 ሔክታር መሬት ላይ ልዩ ልዩ የግብርና ስራዎች እያከናወኑ መሆኑንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.