የኢድ አል አድሃ በዓል በሰላም እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል – የደቡብ ክልል ፖሊስ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል 1 ሺህ 443ኛው የኢድ አል አድሃ(አረፋ) በዓል በሰላም እንዲከበር አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነትና ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ረዳት ኮሚሽነር ጁሃር ሙሳ÷ በክልሉ የሚገኙ የጸጥታ አካላት ከሃይማኖት መሪዎችና አባቶች ጋር በመተባባር የቁጥጥር፣ የፍተሻና ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲኖር በመስራት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በበዓሉ ዕለት ለታዳሚዎች መንገድ የማስከፈት፣ የተጓዦች ንብረትና ተሽከርካሪ እንዳይጠፋና እንዳይሰረቅ ክትትልና ጥበቃ ይደረጋል ብለዋል።
ምዕመኑ በዓሉን ተሰባስበው በሚያከብሩባቸው አካባቢዎች የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይኖር የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶች መከናወናቸውንም ረዳት ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
ሕዝበ ሙስሊሙና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች ወንጀልና ለደህንነት አጠራጣሪ የሆኑ ነገሮች ሲያጋጥሙ ለአካባቢው ፖሊስ ጥቆማ እንዲሰጡ ረዳት ኮሚሽሩ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
1 ሺህ 443ኛው የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ነገ ይከበራል።
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!