Fana: At a Speed of Life!

ሕዝበ ሙስሊሙ የዒድ አል አደሃ (አረፋ) በዓልን ሲያከብር ለሀገር ሰላም በመጸለይ ሊሆን ይገባል- አቶ አሻድሊ ሀሰን

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሕዝበ ሙስሊሙ የዒድ አል አደሃ በዓልን ሲያከብር ለሀገር ሰላም በመጸለይ ሊሆን እንደሚገባ የቤኒሻጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ገለጹ፡፡
1443ኛው የዒድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ በርካታ የሃይማኖቱ ተከታዮች በተገኙበት በሶላትና በጸሎት ተከብሯል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በበዓሉ አከባበር ስነ ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የዒድ አል አደሃ (አረፋ) በዓል የፍቅርና የመስዋዕትነት በዓል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሀገርን ሰላምና ልማት የማይፈልጉ ኃይሎች አሁንም የጥፋት ሥራቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን ጠቁመው÷ መላው የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ለሀገራቸው ሰላም ጸሎት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጠሩ ችግሮችንና በንጹሃን ዜጎች ላይ እየደረሱ ያሉ ጥቃቶችን ለማስቆም የሃይማኖት አባቶች ትክክለኛውን የእምነቱን አስተምሮ በማስተማር አባታዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል፡፡
ሰላም ከሌለ እንደዚህ በጋራ ተሰብስቦ መስገድና ጸሎት ማድረግ አይቻልም ያሉት አቶ አሻድሊ÷ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ከሌሎች ሃይማኖት ተከታዮቸ ጋር የበለጠ በመተባበር ለሀገር ሰላም መስፈን የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
ወጣቶችም ከእኩይ ተግባራት ራሳቸውን በመጠበቅ ትክክለኛውን የሃይማኖት አስተምህሮ ከአባቶች መረዳትና መተግበር ይጠበቅባቸዋል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
የክልሉ የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ም/ቤት ተወካይ ሼህ አልባቅር አፃዲቅ መዕመኑ፣ የሃይማኖቱ ተከታዮች በዓሉን በመረዳዳትና በመደጋገፍ ሊያከብሩት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.