Fana: At a Speed of Life!

የሞጆ-ሀዋሳ ፈጣን መንገድ የግንባት ሂደት በወሰን ማስከበር ችግር እየተስተጓጎለ መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣መጋቢት 1፣2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ከሞጆ -ሀዋሳ እየተገነባ ላለው ፈጣን መንገድ የወሰን ማስከበር ችግር ለግንባታ ሂደቱ ፈተና መሆኑ ተገልጿል።

የመንገዱ ግንባታ በ2008 ዓ.ም የተጀመረ ቢሆንም አሁን ላይ በሚፈለገው ልክ ፈጣን የግንባታ እንቅስቃሴ ላይ አለመሆኑ ቅሬታ አስነስቷል።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የሚያሰራው ይህ የመንገድ ፕሮጀክት በአራት ምዕራፎች ተከፍሎ ግንባታው እየተከናወነ ይገኛል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ባደረገው ቅኝት የመንገዱ ግንባታ የመጀመሪያ ምእራፍ የሆነው ከሞጆ – መቂ 56 ኪሎ ሜትር ፈጣን ሂደት ላይ መሆኑን ተመልክቷል።

የመንገዱ ግንባታ 6 ኪሎ ሜትር ብቻ የቀረው መሆኑን የተናገሩት አማካሪው፥ በቀጣይ አምስት ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል።

በዴዎ ኢንጂነሪንግ እና ኮንስትራክሽን እየተሰራ የሚገኘው 37 ኪሎሜትር የሚረዝመው የመቂ -ዝዋይ መስመር ደግሞ 29 ኪሎ ሜትር የሚሆነው የመንገዱ ግንባታ መጠናቀቁን ኮንትራክተሩ ሉ ኪ ዮንግ ተናግረዋል ።

አጠቃላይ የመንገድ ሽፋኑ 79 በመቶ መድረሱን የገለጹት ሃላፊው፥ የወሰን ማስከበር ችግር ቀዳሚው ፈተና መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሆኖም እስከ ፈረንጆቹ 2021 ድረስ ግንባታውን አጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ለማድርግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ከዝዋይ -አርሲ ነጌሌ ያለው መስመር ከፍተኛ የሆነ የመጓተት ችግር ያለበት መሆኑ ተመላክቷል።

57 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ይህ መንገድ ኤስ ቢ አይ ኢንተርናሽናል ሆልዲንግ በተሰኘ የግንባታ ተቋራጭ ነው እየተከናወነ የሚገኘው።

ይሁን እንጂ የካቲት 2010 ዓ.ም የተጀመረው የመንገዱ ግንባታ በወሰን ማስከበር ምክንያት 6 በመቶ ብቻ መጠናቀቁ ነው የተገለጸው።

የፕሮጀክቱ ምክትል አማካሪ የሆኑት አቶ ካሳሁን በቀለ እንደገለጹት፥ ፕሮጀክቱ የግብዓት ማከማቻ ስፋራ በማጣቱ ምክንያት ስራውን በተገቢው ሁኔታ ማከናወን አልተቻለም።

በወሰን ማስከበር ውዝግብ ምክንያትም ከፍተኛ የሀገር ሃብት እየባከነ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ካሳሁን፥ የዲዛይን ማሻሻያ ጭምር ቢደረግም በአካባቢው አስተዳደር ትብብር ማጣት ተጽዕኖ መፈጠሩን ተናግረዋል ።

የኦሮሚያ ክልል መንገዶች ባለስልጣን ሃላፊ ኢንጂነር ደረጀ ፍቃዱ በበኩላቸው፥በክልሉ በሚገነባው የፈጣን መንገድ ጋር በተያያዘ ለሚነሱ የወሰን ማስከበር ችግሮች ፈጣን ምላሽ እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዝዋይ – አርሲ ነጌሌ መስመር ለተነሳው ቅሬታም ምላሽ ለመስጠት ነገ ጉዳዩን የሚያጣሩ ባለሞያዎች ወደ ስፋራው የሚላኩ መሆኑን ጠቁመዋል።

በወሰን ማስከበር ምክንያት የሚስተጓጎሉ የፈጣን መንገዱ አካባቢዎች ላይ በቀጣይም ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

በሃይለኢየሱስ መኮንን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.