Fana: At a Speed of Life!

የኦሞራቴ – ኦሞ ድልድይ – ኛንጋቶም- ካንጋተን የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በተያዘለት ጊዜ እየተካሄደ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) 64 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የኦሞራቴ – ኦሞ ድልድይ – ኛንጋቶም- ካንጋተን የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በተያዘለት የጊዜ ገደብ እየተካሄደ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ፡፡
በመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን የገለጸው አስተዳደሩ÷ ከእነዚህ መካከል የምንጣሮ፣ የልል አፈር ቁፋሮ፣ የአፈር ሙሌት እንዲሁም በርካታ የስትራክቸር ስራዎች መሠራቸውን አስታውቋል፡፡
የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ሌየር የአስፋልት ስራዎችም መጠናቀቃቸው እና የዋና አስፋልት የሙከራ ስራ ተጠናቆ የአስፋልት ኮንክሪት ስራው በጅምር ላይ እንደሚገኝ ተመላክቷል።
ፕሮጀክቱ ኦሞራቴ ከተማ ላይ ጀምሮ ካንጋታን ከተማ ላይ የሚጠናቀቅ ሲሆን÷ መንገዱ በገጠር 10 ሜትር፣ በከተማ 19 ሜትር እና በወረዳ 19 ሜትር ስፋት ያለው ሆኖ እየተገነባ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር መረጃ ያመላክታል፡፡
ለመንገዱ ግንባታ የተበጀተው 965 ሚሊየን 890 ሺህ 930 ብር ከ37 ሳንቲም ሲሆን ወጪውም በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ነው፡፡
የመንገድ ግንባታው ሲጠናቀቅ÷ ቀደም ሲል የነበረውን የጉዞ እርዝማኔ በ2 ሰአት እንደሚቀንስ እና በአካባቢው የሚገኘውን ከፊል አርብቶ አደርና ከፊል አርሶ አደር ማህበረሰብን መሰረታዊ ፍላጎት ተደራሽ እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.