በሁመራ ከተማ በጦርነት ለተጎዱ ነዋሪዎች ከ12 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ማኅበራዊና ልማት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ከካሪታስ ስዊዘርላንድ በጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በመተባበር በሁመራ ከተማ በጦርነት ለተጎዱ ነዋሪዎች ድጋፍ አድርጓል፡፡
በካሪታስ ስዊዘርላንድ በጎ አድራጎት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ኅላፊ ሪናቶ ሜሌ÷ ድርጅታቸው በተለያዩ ቦታዎች በመገኘት በጦርነቱ ለተጎዱ የማኅበረሰብ አባላት የሰብዓዊ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል።
ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ከባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ማኅበራዊና ልማት ጽሕፈት ቤት ጋር በመተባበር ከ12 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ በማድረግ የቤት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገናል ብለዋል።
የክረምት ወቅት እንደመሆኑ መጠን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ በማድረግና የተቸገሩትን በመርዳት የበኩሉን ኀላፊነት ሊወጣ ይገባል ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ ልማት ኮሚሽን የባሕር ዳር ደሴ ሰበካ የፕሮግራም ማናጀር ኀላፊ አቶ ብርሃኑ ፈቃዱ በበኩላቸው÷ ከጦርነቱ ማግስት ቤተ ክርስቲያኗ በጦርነቱ ለተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተለያየ ድጋፍ ስታደርግ መቆየቷን አስታውሰዋል፡፡
በሁመራ ከተማ በጦርነቱ ለተጎዱና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ከ1 ሺህ 700 በላይ ሰዎች የቤት ውስጥ የቁሳቁስ ድጋፍ አድርገናል ነው ያሉት።
ሰብዓዊነት ዘር ቀለም አይለይምና የሃይማኖት ተቋማት ፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ከመንግሥት ጋር በመሆን በጦርነቱ ለተጎዱና ቤት ንብረታቸውን ላጡ ወገኖች ድጋፍ በማድረግ የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባልም ብለዋል።
ድጋፍ የተደረገላቸው ዜጎችም መንግሥት በአካባቢው የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ በመገንባትና ማኅበረሰቡን ከተረጅነት በማላቀቅ የሥራ እድል ሊፈጥር እንደሚገባ መጠየቃቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡