የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የ15 ዓመት የጤና ኤክስቴንሽን ፍኖተ ካርታ አዘጋጀ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለዜጎች የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት ያሻሽላል ያለውን የ15 ዓመት የጤና ኤክስቴንሽን ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀቱን የክልሉ የጤና ቢሮ አስታወቀ።
ፍኖተ ካርታውን የሚያስተዋውቅ የውይይት መድረክ በዛሬው ዕለት በአሶሳ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ፈቃዱ ረጋሳ÷ፍኖተ ካርታው ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ ሲተገበር የቆየው የጤና ኤክስቴሽን ፕሮግራም ቀጣይ ምዕራፍ መሆኑን ገልጸዋል።
በፕሮግራሙ በሽታን ለመከላከል በተከናወኑ ስራዎች የሕብረተሰቡ በተለይም የሴቶችና ሕጻናት ጤና መሻሻል አሳይቷል ብለዋል።
ይሁንና በየደረጃው የሚገኙ የክልሉ አመራሮች ለፕሮግራሙ ክትትልና ድጋፍ በሚፈለገው መጠን ባለማድረጋቸው በአተገባበሩ ላይ ችግሮች እንዳጋጠመ ነው ያመላከቱት።
በመሆኑም በፕሮግራሙ ላይ ማሻሻያ በማድረግ የጤና ኤክስቴንሽን ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
አቶ ፈቃዱ ፍኖተ ካርታው ለሰው ኃይል አቅም መሻሻል ትኩረት መስጠቱን ገልጸው÷ የጤና ኬላዎች ውህድ መሰረታዊና አጠቃላይ በሚል የአደረጃጀት ለውጥ እንደተደረገባቸው አስረድተዋል።
ፍኖተ ካርታውን ከ2015 በጀት ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስፈልጉ የዝግጅት ስራዎች እንደተጠናቀቁ መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ከጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በተጨማሪ ነርሶች፣ የጤና መኮንኖችና የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች በፍኖተ ካርታው ትግበራ እንደሚሳተፉ ገልጸው፤ ባለድርሻ አካላትም ድጋፍና አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚኖርባቸው አመልክተዋል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!