የትምህርት ዘርፉን ብቃት ባለው የሰው ኃይል ለመገንባት እንደሚሠራ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ገለጹ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የትምህርት ሚኒስቴር ዘርፉን ብቃት ባለው የሰው ኃይል ለመገንባት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ገለጹ።
ሚኒስቴሩ ለተቋሙ አመራሮችና ሠራተኞች በለውጥ አመራር፣ ተቋማዊ ስነ ምግባር ፣ በውሳኔ አሰጣጥ እና ተግባቦት ላይ ስልጠና እየሰጠ ነው፡፡
ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ በስልጠናው ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የትምህርት ዘርፉን ለመምራት በሙያ ብቻ ሳይሆን በአስተሳሰብም ብቁ መሆን ይገባል ብለዋል፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር ሠራተኞች ትውልድን የማፍራት ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተገንዝበው÷ ስራቸውን በጥራትና በብቃት መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡
የተሻለና ማህበረሰቡ የሚኮራበት የትምህርት ተቋም መኖር ለሕዝብና ለመንግስት ብቻ ሳይሆን÷ ለሰራተኛውም አስፈላጊ መሆኑንም ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡
ሠራተኛው የሚሠራበትን ተቋም የሚወድ፣ ስራዎችን አክብሮ የሚሠራና ዕውቀቱንም በወረቀት ብቻ ሳይሆን በተግባር የሚመዘን ሊሆን እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ለሁት ቀናት የሚካሄደው ስልጠና÷ በውጭ ሀገርና በሀገር ውስጥ በትምህርት ዘርፍ ከፍተኛ ልምድና ዕውቀት ባላቸው ከፍተኛ የዘርፉ ባለሙያዎች እየተሰጠ መሆኑን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል፡፡