ሶማሌ ክልል በበጀት ዓመቱ 7 ነጥብ 26 ቢሊየን ብር ገቢ መሠብሰብ መቻሉ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) ሶማሌ ክልል በ2014 በጀት ዓመት ከገቢ ግብር 7 ነጥብ 26 ቢሊየን ብር መሰብሰብ መቻሉን የሶማሌ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ ገለጹ፡፡
ክልሉ በበጀት ዓመቱ በድርቅ እና በሌሎች ችግሮች በመፈተኑ ለመሰብሰብ ያቀደውን 7 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ገቢ ግብር ማሳካት እንዳላስቻለ የተገለጸ ሲሆን፤ የዕቅዱን 95 ነጥብ 5 በመቶ አፈጻጸም ማለትም 7 ነጥብ 26 ቢሊየን ብር ግን መሠብሰብ እንደቻለ አቶ ሙስጠፌ መሀመድ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው አመላክተዋል፡፡
አቶ ሙስጠፌ ÷ ባለፉት አራት የለውጥ ዓመታት ብቻ 18 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ገቢ እንደ ተሰበሰበ የጠቆሙ ሲሆን ይህም ከለውጡ በፊት ከነበሩት 10 ዓመታት የ10 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
ሁኔታው የክልሉ መንግስት የመፈጸም አቅም መጠናከሩን እንደሚያሳይ አያየዘው ገልፀዋል።
እየተካሄደ ባለው የክልሉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሥራ አፈፃፀም ግምገማ ላይ የክልሉ የገቢዎች ቢሮ የአፈፃፀም ሪፖርት ቀርቧል።