ዓለምአቀፋዊ ዜና

ፕሬዚዳንት ፑቲን እና ኤርዶኻን በሁለትዮሽ እና በዩክሬን ወቅታዊ ሁኔታ በስልክ ተወያዩ

By Alemayehu Geremew

July 12, 2022

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በኢኮኖሚያዊ ትብብር እድገት እና በዩክሬን ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ከቱርኩ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ታይፕ ኤርዶኻን ጋር በስልክ ተወያይተዋል።

መሪዎቹ የሀገራቱን ኢኮኖሚያዊ ትብብር እና የንግድ ልውውጥን ማሳደግ፣ የኮንትራት የህግ ማዕቀፎችን ለማሻሻል እንዲሁም በሀገር ውስጥ ምንዛሬ መገበያያት በሚቻልባቸው አግባቦች ላይ ትኩረታቸውን አድርገው መክረዋል።

ከዚህ ባለፈም ሩሲያ የሃይል አቅርቦቷን ሳታቋርጥ ማቅረብ በምትችልበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውን ሺንዋ ክሬሚሊንን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

መሪዎቹ በሀገራቱ የሁለትዮሽ ትብብር ዙሪያተቀራርበው ለመስራት መስማማታቸውንም ነው ዘገባው ያመላከተው።

ከዩክሬን ጋር በተያያዘም የጥቁር ባህርን መስመር ደህንነት ማስጠበቅ ብሎም የጥራጥሬና የእህል ምርቶችን ለዓለም አቀፉ ገበያ ማድረስ በሚቻልበት አግባብ ላይ ስለሚኖራቸው ትብብር መምከራቸውንም ዘገባው አመላክቷል።

ኤርዶኻን በዚህ ወቅት ሀገራቸው በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ያለውን የድርድር ሂደት ለማስጀመር በሚደረገው ጥረት ሁሉንም ዓይነት ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ናት ማለታቸውን የቱርክ ፕሬዚዳንት ፅህፈት ቤት አስታውቋል።