ሩሲያ በዩክሬን ለተፈፀመባት ጥቃት አሜሪካን ተጠያቂ አደረገች
አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡባዊ ዩክሬን በሩሲያ ስር በምትገኘው ኖቫያ ካክሆቭካ ከተማ የተፈጸመው የሰኞው ጥቃት ያለ አሜሪካ እርዳታ ሊከሰት አይችልም ሲሉ አንድ ከፍተኛ የሩሲያ ዲፕሎማት ተናግረዋል።
በተባበሩት መንግስታት የሩሲያ ተልዕኮ ምክትል ኃላፊ ዲሚትሪ ፖሊያንስኪ ለሪያ ኖቮስቲ እንደተናገሩት አሜሪካ ለኪየቭ የምታደርገው ከባድ የጦር መሳሪያዎች ድጋፍ አካባቢውን እንድትመታ አቅም ሰጥቷታል ብለዋል።
ጥቃቱ የአሜሪካ ለኪየቭ የምታደርገው የጦር መሣሪያ ድጋፍ ያስከተለው ውጤት ነው ያሉት ዲፕሎማቱ፥ በንፁሃን መኖሪያ አካባቢዎች ላይ የሚደረጉ ጥቃቶች ውግዘት እንጂ ሌላ የሚያስገኙት ትርፍ የለም ሲሉም ገልጸዋል።
የከተማው አስተዳደር ኃላፊ የሆኑት ቭላድሚር ሊዮንቴቭ ዛሬ እንደተናገሩት በጥቃቱ ሰባት ሰዎች ሲገደሉ እስከ 70 የሚደርሱ ደግሞ ቆስለዋል።
ቀደም ሲል በተፈፀመ ጥቃት የማዳበሪያ ማከማቻ መፈንዳቱንና በርካታ ቤቶች እንዲሁም ገበያና ሆስፒታልን ጨምሮ ሌሎች ቦታዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል በከተማዋ የሚገኘውን ምግብ ጨምሮ 35 ቶን የእርዳታ ቁሳቁስ በውስጡ የያዘ መጋዘንም ወድሟልም ነው ያሉት።
የዩክሬን ጦር በዛሬው ዕለት በኖቫያ ካክሆቭካ የሚገኘውን የጥይት መጋዘን ማውደሙን አስታውቋል።
ጥቃቱን የኪየቭ ደጋፊዎች በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው በሰፊው አጋርተውታል።
ዩክሬን እና ሩሲያ መኖሪያ አካባቢዎችን በመደብደብ እና ሰላማዊ ዜጎችን በመግደል እርስ በርስ በተደጋጋሚ ሲወነጃጀሉ መቆየታቸውን አር ቲ በዘገባው አስታውሷል።