ግብረ ኃይሉ በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጸሙ የሰብዓዊ ጥሰቶችን ለመመርመር ሦስተኛ ስብሰባውን እያካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ሀምሌ 6 ፣2014 (ኤፍ ቢሲ) በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመመርመር የተቋቋመው የሚኒስትሮች የጋራ ግብረ ኃይል ሦስተኛ ስብሰባውን እያካሄደ ነው።
ስብሰባው ሁለት ዓበይት ነጥቦችን እንደሚዳስስ የተመለከተ ሲሆን ፥ ባለፉት ጊዜያት የተከናወኑ የግብረኃይሉ ሥራዎች እና ያጋጠሙ ችግሮች ላይ ሪፖርት ቀርቦ ውይይት በማድረግ ቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎች ይቀመጣሉ ተብሏል።
በመቀጠል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከፍተኛ ጽኅፈት ቤትና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት የጋራ ምርመራ ቡድን ባቀረቡት የምርመራ ምክረ-ሃሳብ መሠረት የሽግግር ፍትህ ረቂቅ ፖሊሲ ሠነድ ላይ ይመክራልም ተብሏል፡፡
ግብረ ኃይሉ ÷ በአማራ፣ በትግራይ እና በአፋር ክልሎች የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን አስመልክቶ የተሟላ የወንጀል ምርመራ በማካሄድ አጥፊዎችን በኅግ ተጠያቂ ለማድረግና ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም የተደራጀ ነው።
በይስማው አደራው