ጤና

የበቆሎ የጤና ጥቅሞች

By ዮሐንስ ደርበው

July 13, 2022

 

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቆሎ መመገብ ከመደበኛ የምግብነት ጥቅሙ ባሻገር በርካታ ትሩፋቶች እንዳሉት የጤና እና የሥነ-ምግብ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡

በቆሎ በአሰር (ፋይበር) የበለፀገ በመሆኑ በቆሎን መመገብ ለሆድ ድርቀት እና ተያይዞ ሊከሰት ከሚችለው የኪንታሮት ሕመም እንዲሁም የፊንጢጣ ካንሰር የመጋለጥ ዕድልን እንደሚቀንስ ተጠቁሟል፡፡

በቆሎ ለአጥንት ጥንካሬና ዕድገት ብሎም ለልብ ጤና ጠቀሜታ ያላቸውን ፎስፈረስ እና ማግኒዢየም የተባሉ ንጥረ-ነገሮችን በበቂ መጠን እንደያዘም የሥነ-ምግብ እና ጤና ባለሙያዎች ይጠቅሳሉ፡፡

በቆሎ መመገብ የማይመከረውን የኮሌስትሮል ዓይነት ለመቀነስ እንደሚረዳ እና ከፍተኛ የኮሌስትሮል መጠንን ተከትሎ በሚመጡ ሕመሞች እንዳንጠቃ እንደሚያደርግም ተነግሯል፡፡

በቆሎ በቫይታሚን ቢ በተለይም በታያሚን የበለፀገ በመሆኑ ለነርቭ ጤና ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ተገልጿል፡፡

በቆሎ የ“አንቲኦክሲደንት” ባህሪ ስላለውም ካንሰርን የመከላከል አቅም እንዳለው የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

በቆሎን መመገብ ለዓይን ጤና፣ የደም የስኳር መጠን ለመቆጣጠር፣ አኒሚያን “ ደም ማነስን ” ለማከም፣ እንዲሁም ለሰውነታችን አስፈላጊ የሆኑ “አሚኖ አሲዶችን” ለማግኘት እና አመጋገባችንን ከ”ግሉተን”-ነጻ ለማድረግ ይመከራልም ተብሏል።

100 ግራም የተቀቀለ ቢጫ በቆሎ በውስጡ፥ 96 ካሎሪ፣ 73 በመቶ ውሃ፣ 3 ነጥብ 4 ግራም ፕሮቲን፣ 21 ግራም ካርቦሃይድሬት፣ 4 ነጥብ 5 ግራም ስኳር፣ 2 ነጥብ 4 ግራም አሰር (ፋይበር) እንዲሁም 1 ነጥብ 5 ግራም ቅባት እንደሚይዝ ኸልዝ ላይን አስነብቧል፡፡