የመዲናዋን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅና ወንጀልን ለመከላከል ቁጥጥር እየተደረገ ነው -ፖሊስ
አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅና የወንጀል ድርጊቶችን ለመከላከል ጠንካራ ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገለጸ።
የአዲስ አበባ ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ÷ በመዲናዋ የተለያዩ ወንጀሎች እንደሚፈፀሙ ገልጸው ወንጀሎችን ለመቀነስ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በተለይም ወቅቱ ክረምት እንደመሆኑ በዚህ ወቅት የሚፈፀሙ የወንጀል ዓይነቶችን በመለየት እርምጃ ለመውሰድና ወንጀሎችን ለመከላከል ልዩ እቅድ ወጥቶ ወደ ተግባር መገባቱን ጠቅሰዋል።
ህብረተሰቡ የወንጀል ድርጊቶች በሚያጋጥሙት ወቅት ሊያደርገው ስለሚገባ ጥቆማና ስለሚተገበሩ እርምጃዎች ግንዛቤ የመስጠት ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
ከፀጥታ አንፃር አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲኖሩ ህብረተሰቡ ለየአካባቢው የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት መረጃ የሚሰጥበት ትስስር መፈጠሩንም ጠቁመዋል።
በከተማዋ በትራፊክ መብራቶችና በመንገድ ዳር ጎዳና ተዳዳሪ መስለው የቅሚያ ወንጀሎችን የሚፈፅሙ ግለሰቦች መኖራቸውንም ነው የገለጹት።
ፖሊስ በከተማዋ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመከላከልና ተፈፅመው ሲገኙም እርምጃ ለመውሰድ ጠንካራ የቁጥጥር ስራ ማድረግ የሚያስችለውን ዝግጅት አድርጎ ወደ ዘመቻ መግባቱን ጠቅሰዋል።
አዲስ አበባን የሽብር ማዕከል ለማድረግ ያሰቡ አካላትን ሴራ ህብረተሰቡ ከፖሊስ ጋር በመሆን ማምከኑ አንዱ ማሳያ እንደሆነ ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በክረምት ወቅትም የፀጥታ ችግሮችንና የወንጀል ድርጊቶችን ለመከላከል ህብረተሰቡ መረጃዎችን ለፖሊስ በመስጠት የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግ ጠይቀዋል።