በአሸባሪው ሸኔ ላይ እየተወሰደ ባለው እርምጃ ቡድኑን ማዳከም ተችሏል – የመንግስት ኮሙኒኬሽን
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሸባሪው ሸኔ ላይ እየተወሰደ ባለው እርምጃ ቡድኑን ማዳከም መቻሉን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለፀ፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ በሰጡት መግለጫ ÷መንግስት ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጅት በአሸባሪው ሸኔ ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
መንግስት በሸኔ ላይ እየወሰደ ባለው እርምጃም ቡድኑ መዳከሙን እና ሸሽቶ ወደ ጎረቤት ሀገራት መደበቁን ገልፀዋል፡፡
ይሁን እንጅ የውሸት መረጃዎችን በመልቀቅ እና ለጥፋት ሀይሉ ሽፋን በመስጠት በህዝቦች ዘንድ መጠራጠር እንዲኖር የሚያደርጉ ግሰቦች መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡
በምዕራብ ወለጋ ጥቃት ለደረሰባቸው ዜጎችም መንግስት አስፈላጊውን የሰብአዊ ደጋፍ እርዳታእያደረገ መሆኑንም ነው ሚኒስትር ዴኤታው የገለፁት፡፡
የአሸባሪዎቹ አላማ ከውጭ ባንዳዎች ጋር በመተባበር ህዝቡ በመንግስት ላይ ተስፋ እንዲቆርጥ ማድረግ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ህብረተሰቡ ከመንግስት ጋር በመቆም የህግ ማስከበር ዘመቻውን እንዲያግዝ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከህግ ማስከበር ተግባሩ በተጨማሪ ሃላፊነታቸውን መወጣት ሲገባቸው በመንግስት መዋቅር ስር ሆነው በተለያዩ የሙስና ወንጀሎች የተሳተፉ ባለስልጣናትን ተጠያቂ የማድረግ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልፀዋል፡፡
የሰሜኑን ግጭት በተመለከተ በሰጡት መግለጫም÷ መንግስት ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሰላም እንቅስቃሴ መጀመሩን እና የሰላም ተደራደሪ ቡድን ተዋቅሮ ወደስራ መግባቱን አብራርተዋል፡፡
ይሁን እንጅ በህወሓት በኩል የተወሰደ የሰላም እርምጃ አለመኖሩን እና ቡድኑ አሁንም ዜጎችን በመመልመል ወደ ጦርነት ለመግባት እየተዘጋጀ መሆኑንም ነው ሚኒስትር ዴኤታው የገለፁት፡፡
የቀረቡትን የሰላም አማራጮች ወደ ጎን ማለቱ ቡድኑ ያለጦርነት መኖር እንደማይችል ማሳያ መሆኑንም ሚኒስትር ዴአታው በሰጡት መግለጫ አብራርተዋል፡፡