Fana: At a Speed of Life!

በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ የነበረውን አብሮነት አጠናክሮ ለማስቀጠል የእርቀ ሰላም ኮንፍረስ ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ እና አካባቢው የተገኘውን ሰላም አጠናክሮ ለማስቀጠል በቡለን ወረዳ ህዝባዊ እርቀ ሰላም ኮንፍረስ ተካሂዷል።
በእርቀ ሰላም ኮንፍረሱ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰላም ግንባታና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ ዶክተር አቢዮት አልቦሮን ጨምሮ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች፣ የክልል፣ የዞን እንዲሁም የአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
ዶክተር አቢዮት አልቦሮ፥አሁን ላይ እየተካሄደ ያለውን ህግ የማስከበር ተግባር ተከትሎ የተገኘውን ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል ”ያለፈውን በደል በይቅርታና በእርቅ” በመፍታት አንድነትን እና አብሮነትን መመለስ የሁላችንም ድርሻ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
የሰው ልጅ ሲኖር ግጭቶችና አለመግባባቶች ሊከሰቱ ይችላሉ፤ነገር ግን የህይወት ቀጣይነትን በመገንዘብ የግጭት መንስኤዎችን በመለየት ያለፈውን በይቅርታና ምህረት መጋረጃ በመዝጋት መጻኢ እድሎችን በመቻቻልና በመከባበር አብሮ መኖር መቻል የብልህና ሀገር ወዳድ ማህበረሰብ መገለጫ መሆኑን በመገንዘብ ለሰላም ዘብ መቆም አስፈላጊ መሆኑን አውስተዋል፡፡
የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጋሹ ዱጋዝ በበኩላቸው÷ ቀጠናው የልማት ኮሪደር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተለያዩ ፍላጎት ያላቸው የውስጥ እና የውጭ ሃይሎች ክንዳቸውን የሚያሳርፉበት አካባቢ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በቀጣናው የሚስተዋሉ ችግሮችን በመመከት የብልጽግና ጉዟችንን ማሳካት የሚቻለውም በአንድነት ስንቆም ብቻ ነው ማለታቸውን ከመጸከል ዞን ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
መንግስት የህዝቡን የሰላምና የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እያካናወነ ያለውን ተግባር ከዳር ለማድረስ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች አስተምሮ የጎላ ድርሻ እንዳለው ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል።
የቡለን ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ግዛቱ ባልዳ ደግሞ በቀጠናው የተገኘውን ሰላም አጠናክሮ ለማስቀጠል በቀበሌ ማዕከላት ሲካሄድ በነበረው ህዝባዊ ኮንፍረስ የተገኙ መልካም አስተያየቶችን ለማስቀጠል እርቀ ሰላሙ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
አሁን ባለው ሰላም ተፈናቅለው የነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎች መመለስ መጀመራቸውን ነው ዋና አስተዳዳሪው የተናገሩት፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.