Fana: At a Speed of Life!

እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች መዘግየት ሰብዓዊ ድጋፍ በወቅቱ እንዳይደርስ እንቅፋት ፈጥሯል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች በመንገድ ላይ በሚያጋጥማቸው መዘግየት ለተፈናቀሉ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ በወቅቱ ለማድረስ መቸገሩን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የክልሉ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር ታረቀኝ ታሲሳ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፥ በክልሉ በሦስት ዞኖችና አንድ ልዩ ወረዳ 442 ሺህ 106 የሚጠጉ ዜጎች በተለያዩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ምክንያቶች ከቀያቸው ተፈናቅለው ሠብዓዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡

በመተከል ዞን ለሚገኙ ተፈናቃዮች በተቆራረጠ መንገድም ቢሆን ሠብዓዊ ድጋፍ በተሻለ ሁኔታ እየቀረበ መሆኑን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ ፥ በሌሎቹ አካባቢዎች ግን እርዳታ በጫኑ ተሽከርካሪዎች በመንገድ ላይ በሚፈጠር መዘግየት ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎች ሠብዓዊ ድጋፍ በወቅቱ ለማድረስ አስቸጋሪ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ሠብዓዊ እርዳታ ጭነው ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚመጡ ተሽከርከርካሪዎች ከ20 እስከ 30 ቀናት በመንገድ ላይ እንደሚቆዩ ነው የተናገሩት ፡፡

በአሁኑ ወቅትም በዚሁ የጸጥታ ችግርምክንያት ከ10 በላይ ተሳቢዎች በጊምቢ ከተማ እንዲቆሙ ተደርገዋል ብለዋል ኮሚሽነሩ፡፡

ከፌዴራል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ሰብዓዊ ድጋፍ ይዘው ለቀናት የቆሙ ተሸከርካሪዎች በእጀባም ማስገባት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ዙሪያ ከኦሮሚያ ክልል መንግስትና ከመከላከያ ኮማንድ ፖስት ጋር መነጋገራቸውን ገልጸው ፥ ሰሞኑን መፍትሔ ያገኛል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡

በተለይም በካማሺ ዞን ለሚገኙ ተፈናቃዮች በዚሁ ችግር ምክንያት ከሚያዚያ 9/2014 ዓ.ም ጀምሮ ሠብዓዊ ድጋፍ በተገቢው ሁኔታ አለመድረሱን ኮሚሽነር ታረቀኝ ተናግረዋል፡፡

ይህንን ችግር ለመፍታትም የፌዴራል አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ለካማሺ ዞን በዓለም የምግብ ፕሮግራም በኩል ድጋፍ ማቅረብ እንዲችል ጥያቄ ቀርቧል ማለታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.