Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ በበጀት ዓመቱ ከ405 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ተፈጥሯል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በበጀት ዓመቱ ለ405 ሺህ 536 ዜጎች የሥራ እድል መፈጠሩን የከተማዋ ከንቲባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

ከንቲባዋ የሥራ እድል ፈጠራን አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር ፥ በበጀት ዓመቱ ለ350 ሺህ ዜጐች አዳዲስ አማራጭ የሥራ ዕድል መስኮችን ለመለየት ታቅዶ፥ ከ391 ሺህ በላይ (112 በመቶ) የሥራ እድል መፍጠር የሚያስችሉ ልዩ ልዩ የሥራ መስኮች መለየታቸውን ገልጸዋል፡፡

ለ350 ሺህ ሥራ ፈላጊዎች የሥራ እድል ለመፍጠር በተደረገው ርብርብ 405 ሺህ 536 ዜጎች ሥራ ማግኘታቸውን ነው የተናገሩት፡፡

ከነዚህ ውስጥ 380 ሺህ 720 ቋሚ የሥራ እድል ሲሆን ፥ 24 ሺህ 811 ጊዜያዊ የሥራ እድል የተፈጠረላቸው ናቸው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ለ597 አካል ጉዳተኞችና ለ820 ከስደት ተመላሾች የሥራ እድል ተፈጥሮላቸዋል ያሉት ከንቲባዋ ፥ የሥራ እድል ከተፈጠረላቸው መካከል 54 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ሲሆኑ ፤ 76 በመቶ ወጣቶች፣ 16 በመቶ ከዩኒቨርሲቲና ቴክኒክና ሙያ የተመረቁ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በሀገር ውስጥና የውጪ ሀገር የገበያ ትስስር መፍጠርን በተመለከተ ለ21 ሺህ 62 ኢንተርፕራይዞች 6 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር የገበያ ትስስር ለመፍጠር ታቅዶ፥ ለ19 ሺህ 207 ኢንተርፕራይዞች የ8 ቢሊየን ብር የገበያ ትስስር ተፈጥሯልም ነው ያሉት፡፡

የአካል ጉዳተኛ አንቀሳቃሾችን በገበያ ትስስር ተጠቃሚ ለማድረግ ለ320 አንቀሳቃሾች የገበያ ትስስር ለመፍጠር የታቀደ ሲሆን፥ ለ378 የ10 ሚሊየን ብር የገበያ ትስስር መፍጠር መቻሉን ከንቲባ አዳነች ጠቁመዋል፡፡

ከ9 ሺህ 947 ኢንተርፕራይዞች ውስጥ 8 ሺህ 323 ኢንተርፕራይዞች ወደሚቀጥለው ደረጃ እንዲሸጋገሩ መደረጉን መግለጻቸውንም ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በተጨማሪም ተኪ ምርት የሚያመርቱ አምራች ኢንዱስትሪዎችን 568 ለማድረስ ታቅዶ፥ 831 ማድረስ መቻሉንም ነው ያስረዱት፡፡

ከንቲባዋ አክለውም ፥ በሁለተኛው ዙር በምግብ ዋስትናና በልማታዊ ሴፍትኔት መርሐ ግብር በመዲናዋ ለተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመለየት 109 ሺህ 918 ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

በአንድ በኩል በከተማዋ ነዋሪዎች ላይ የኑሮ ውድነት ያስከተለውን ጫና ለመቅረፍ፥ በሌላ በኩል የሥራ አጥነትን ችግር ለመቀነስ የሚያስችል ሥራ ከመሰራት በተጨማሪ የሥራ ባህልን ለማጐልበት ጉልህ አስተዋፅኦ ያለው ተግባር ተከናውኗል ብለዋል ከንቲባ አዳነች፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2014 ዓ.ም. 68 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ገቢ ሰብስቧል፡፡

አፈጻጸሙም÷ የዕቅዱ 100 ነጥብ 3 በመቶ ሲሆን÷ ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም የ21 ነጥብ 13 በመቶ ዕድገት ማሳየቱ ተገልጿል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.