የዳያስፖራ ማህበራት እንደ አገር የተጋረጠብንን ችግር እንድንሻገር አይነተኛ ሚና እየተወጡ ነው- አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በመላ ዓለም የሚገኙ የዳያስፖራ ማህበራት ኢትዮጵያ የገጠሟትን ችግሮች እንድትሻገር አይነተኛ ሚና እየተወጡ መሆናቸውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ተናገሩ፡፡
አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በ”በድር አለማቀፍ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ድርጅት” 22ኛ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ድርጅቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ጉባኤውን በኢትዮጵያ ማድረጉ የሀገር ወዳድነቱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
ሌሎች የዳያስፖራ አደረጃጀቶችም ተመሳሳይ መርሐ ግብራቸውን በኢትዮጵያ እንዲያከናውኑ መነሳሳትን የሚፈጥር ተግባር ነው ብለዋል።
የ”ኢድ እስከ ኢድ” መርሐ ግብር አንዱ አካል የሆነው በድር አለማቀፍ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ድርጅት ጉባኤ ለቀጣይ ቀናት ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን አካቶ በአዲስ አበባ ኤግዚቪሽን ማዕከል እንደሚከናወን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
የ “ከኢድ እስከ ኢድ” ብሄራዊ ኮሚቴ ጣምራ ሰብሳቢና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ እንደገለጹት÷ ጉባኤው ዳያስፖራው ከሀገሩ እርቆ ሲያከናውን የነበረውን ሀገራዊ ተሳትፎ በቅርበት እንዲያከናውን እድል ይሰጣል፡፡
በዚህም ትስስሮችን ለመፍጠር፣ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለመለየት፣ የሀገሪቱን ባህልና ታሪክ ለማወቅ እና ሲመለሱም የቱሪዝም አምባሳደር እንዲሆኑ መድረኩ በጎ አበርክቶ እንዳለው ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እንድሪስ በበኩላቸው÷ የ “በድር ” አባላት ከሀገራቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት በቋሚነት የሚያስጠብቁና በሀገራቸው ጉዳይ ሁሌም ቀድመው የሚገኙ እና አርአያነት ያለው ተግባር የሚፈፅሙ ናቸው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከዳያስፖራ ጋር በምታደርገው ጠንካራ ተሳትፎ ድርጅቱ ትልቅ ድልድይ ነው ብለዋል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!