ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከዓለም አቀፉ የትምህርት አጋርነት ዋና ስራ አስፈጻሚ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከዓለም አቀፉ የትምህርት አጋርነት ዋና ስራ አስፈጻሚ አሊስ ኦልብራይት ጋር ተወያዩ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረጉ ያሉትን ከዓለም አቀፉ የትምህርት አጋርነት ዋና ስራ አስፈጻሚ አሊስ ኦልብራይት በዛሬው እለት ነው በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው ነው ያነጋገሩት።።
በቆይታቸውም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ የዓለም አቀፉ የትምህርት አጋርነት እያደረገ ያለውን ድጋፍ አድንቀዋል።
የዓለም አቀፉ የትምህርት አጋርነት ዋና ስራ አስፈጻሚ አሊስ በበኩላቸው፥ ድጋፋቸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ማረጋገጣቸውን የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።
የዓለም አቀፉ የትምህርት አጋርነት ዋና ስራ አስፈጻሚ አሊስ ኦልብራይት በኢትዮጵያ ቆይታቸው በትናንትናው እለት ከኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጋርም ተገናኝተው ተወያይተዋል።
በተጨማሪም ከትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ጋር የተወያየ ሲሆን፥ በቀጣይም ከከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና ከዓለም ባንክ ተወካዮች ጋር እንደሚወያዩ ይጠበቃል።