ከ30 ዓመታት በፊት ተዘርቶ የነበረው የመለያየት አስተሳሰብ እየጠፋ የወንድማማችነት አስተሳሰብ እንዲተካ እየተሠራ ነው- ዶ/ር ቢቂላ ሁሪሳ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ከ30 ዓመታት በፊት ተዘርቶ የነበረው የመለያየት አስተሳሰብ እየጠፋ የወንድማማችነት አስተሳሰብ እንዲተካ እየተሠራ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለማቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ገለጹ።
የብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ዓለም አቀፍ ግንኙነት በ2014 በጀት ዓመት ያከናወናቸውን ተግባራት በባሕርዳር እየገመገመ ነው።
ከግምገማው ባሻገር የፓርቲው የ2015 የዕቅድ ኦሮንቴሽንም እንደሚያደርግና ለተሳታፊዎቹ ስልጠና እንደሚሰጥ ተመላክቷል።
የፓርቲው የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ÷ የመጠራጠር ትርክት ሳይሆን አንድነት እንዲጠናከርና ወንድማማችነት እንዲጎለብት እየጸሠራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ከሰላሳ ዓመታት በፊት ጀምሮ ተዘርቶ የነበረው የመለያየት አስተሳሰብ እየጠፋ የወንድማማችነት አስተሳሰብ እንዲተካ እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።
የብልጽግና እሳቤዎችን በማስረፅ እና ኢትዮጵያውያንን በብሔራዊ አንድነት የማስተሳሰር ሥራ መሠራቱንም ነው የተናገሩት፡፡
ኢትዮጵያ በሕልውና አደጋ ውስጥ በነበረችበት ጊዜ የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ በብቃት መሥራቱንም አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በጠላቶች እንደማትፈርስና ጠላቶቿን እያፈረሰች እንደምትቀጥል ያረጋገጥንበት ወቅት ነው ያሉት ሃላፊው÷ ያለፈው ዓመት በሰላማዊ መንገድ የመንግሥት ምሥረታ የተደረገ መሆኑንም አስታውሰዋል።
በየአካባቢው ያሉ የፅንፈኝነት እንቅስቃሴዎች ከሕዝብ ተነጥለው እንዲመቱና የሕዝብ አንድነት እንዲጠበቅ የተሠራው የሕዝብ ግንኙነት ሥራ መልካም የሚባል እንደሆነ መግለጻቸውን አሚኮ ዘግቧል።
ኢትዮጵያዊያን የብሔር እና የዘር ፓርቲያቸውን አፍርሰው ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ያለበት ፓርቲ መመስረታቸውና የጋራ ጉባኤ ማካሄዳቸውንም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያውያን ላይ እየተካሄደ ያለውን የሀሰተኛ የሚዲያ ዘመቻን በመመከትና የኢትዮጵያውያን አንድነት እንዲፀና የተሠሩ መልካም ሥራዎች መኖራቸውንም አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያውያን በሀሰተኛ የሚዲያ ዘመቻ እንደማይለያዩ የታየበት መሆኑን ጠቁመው÷ የኢትዮጵያውያንን ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ለመጠበቅ የሚያስችል የሕዝብ ግንኙነት ሥራ እንደሚጠበቅም አሥገንዝበዋል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!