Fana: At a Speed of Life!

በዓመት 8 ነጥብ 1 ሚሊየን ቶን ማምረት የሚችል የሲሚንቶ ፋብሪካ በሸበል በረንታ ሊገነባ ነው

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በዓመት 8 ነጥብ 1 ሚሊየን ቶን ማምረት የሚችል የሲሚንቶ ፋብሪካ በምስራቅ ጎጃም ዞን በሸበል በረንታ ሊገነባ ነው፡፡

 
ከግንባታው ጋር ተይይዞ የከፍተኛ ደረጃ የማዕድን ምርት ስራ ፈቃድ ስምምነት የፊርማ ሥነ ስርዓት በባህርዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
 
በበረንታ ሲሚንቶ ፋብሪካ እና በክልሉ የማእድን ልማት ሀብት ቢሮ መካከል በዛሬው ዕለት በአካባቢው ያለውን ሀብት የመጠቀም እና የምርት ስራ ፈቃድ የፊርማ ስነ ስርዓት እየተካሄደ ይገኛል።
 
በሥነ ስርዓቱ ላይ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ እና የብሔራዊ መረጃ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
 
በክልሉ ብሎም በሀገራችን ያለውን የሲሚንቶ እጥረት ችግር በከፍተኛ ደረጃ ይቀርፋል ተብሎ የሚጠበቀው በረንታ ሲሚንቶ በምስራቅ ጎጃም ዞን በሸበል በረንታ አካባቢ ነው እየተገነባ የሚገኘው፡፡
 
የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ዕቅድ 8 ነጥብ 1 ሚሊየን ቶን በዓመት የማምረት አቅም መገንባት ሲሆን÷ ይህም በሶስት ምእራፎች ተከፍሎ ተግባራዊ እንደሚደረግ ከአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡።
 
በመጀመሪያው የትግበራ ምዕራፍ በቀን 6 ሺህ ቶን ክሊንከር እና በዓመት 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ቶን ሲሚንቶ ማምረት የሚችል ፋብሪካ በ340 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር እየተገነባ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።
 
በአቶ ካሳሁን ምስጋናው እና አቶ ተመስገን ከፍያለው ሀሳብ አመንጪነትና ባለቤትነት የተጀመረው በረንታ ሲሚንቶ በቻይናው ዓለምአቀፍ ተቋራጭ ሲኖማ ሲመንት አማካኝነት ግንባታው እየተከናወነ ሲሆን÷ ፋብሪካው ሲጠናቀቅ በቀን 270 ሺ ኩንታል ሲሚንቶ የማምረት አቅም እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.