Fana: At a Speed of Life!

በዛምቢያ በእስር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደ ሀገራቸው የመመለስ እንቅስቃሴ ሊጀመር ነው

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በዛምቢያ በእስር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደ ሀገራቸው የመመለስ እንቅስቃሴ በዚህ ሳምንት ሊጀመር ነው፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በዛምቢያ ከሚኖሩ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ወኪሎች ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ በዛምቢያ የሚገኙ  የኢትዮጵያውያን በሃገሪቱ ህጋዊ እውቅና ማግኘታቸው የተገለፀ ሲሆን  ሀገርን በመደገፍ  እርስ በርስ ግንኙትን በማጎልበት እና የዜጎችን መብት በማስጠበቅ ለዜጎች እየተንቀሳቀሱ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡

በዛምቢያ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት ከሀገራቸው ኢትዮጵያ ጋር ጥብቅ ቁርኝት እና ተሳትፎ እንዳላቸው የገለፁ ሲሆን ሀገራቸውን በተለያየ መንገድ እየደገፉ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለአብነትም በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋ ለተጓዱ እንዲሁም ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል የገንዘብ እርዳታ በቅርቡ ድጋፍ ማድረጋቸውን የውይይቱ ተሳታፊዎች አንስተዋል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመሄድ በህገወጥ መንገድ የዛምቢያን ድንበር አቋርጠው ሲገቡ በቁጥጥር ስር እየዋሉ ለተለያዩ ችግሮች እየተዳረጉ ይገኛሉ ።

ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የዛምቢያ እስር ቤቶች ውስጥ በእስር ላይ የሚገኙ ሲሆን በጊዜያዊነት እስረኞቹን ለመርዳት የተለያዩ ጥረቶችን እያደረጉ መሆኑን አስረድተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ለተወያዮቹ በሰጡት ምላሽ  የኢትዮጵያ መንግስት ለስደተኞች ጉዳይ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ አስገንዝበዋል፡፡

በተለያዩ ሃገራት እስር ቤቶች  በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ዜጎችን ወደ ሃገር ቤት የማስመለሱ ዘመቻ ተጠኛክሮ መቀጠሉንም ገልፀዋል፡፡

በዛምቢያ በእስር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደ ሃገር ቤት ለመመለስ በዚህ ሳምንት በአፋጣኝ ስራዎች እንደሚጀመሩ አቶ ደመቀ በውይይቱ ወቅት አስታውቀዋል።

እስረኞችን ለመመለስም ከወዲሁም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መጀመራቸውን አቶ ደመቀ መናገራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.