የሐረሪን ባህልና እሴት የመጠበቅና የማልማት ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል- የሐረሪ ብሔራዊ ጉባዔ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐረሪ ቋንቋ፣ ታሪክ፣ ቅርስና እሴቶችን የመጠበቁና የማልማት ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የሐረሪ ብሔራዊ ጉባዔ አሳሰበ፡፡
የሐረሪ ብሔራዊ ጉባዔ 6ኛ ዙር 1ኛ ዓመት 2ኛ መደበኛ ጉባዔውን እያካሄደ ነው፡፡
የሐረሪ ብሔራዊ ጉባዔ ጽሕፈት ቤት ተወካይ አቶ አብዱናስር ኢድሪስ ጉባዔው ከሐረር በተጨማሪ በድሬደዋና በአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽሕፈትቤቶችን ከፍቶ ሰፊ ስራ መስራቱን ጠቁመው÷ በ2014 ምርጫ ወቅት ያጋጠሙ ችግሮችን በመፍታት ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት መቻሉን አስታውሰዋል፡፡
በአጎራባች ክልሎች የሚገኙ የሐረሪ ተወላጆችን በመጎብኘትና እርስ በርስ ግንኙነትን በማጠናከር ረገድ ሰፊ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል፡፡
ጉባዔውም÷ የሐረሪ ቋንቋ፣ ታሪክ፣ ቅርስ እና እሴቶችን የማጠናከር ሥራ በትኩረት እንዲሠራ አቅጣጫ አስቀምጦ የ2014 ሪፖርትን ማጽደቁንም የክልሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል፡፡
ጉባዔው በዛሬ ውሎው የክልሉን ባህል ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ የ2014 በጀት ዓመት አፈፃፀም ሪፖርት አድምጧል፡፡
የዘንድሮውን የሸዋሊድ በዓል በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ከፍተኛ ሥራ መሠራቱ እናየብሔረሰቡን ቅርስ ለመጠበቅ በተደረገው ሥራ 412 ጥንታዊ የእጅ ጽሑፍ ሥራዎች ማሰባሰብና መሰነድ መቻሉ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙክታር ሳሊ በበኩላቸው÷በበጀት ዓመቱ የሐረሪ ቋንቋን ለማሳደግ በአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ የሚሠሩ ሥራዎች የመከታተልና የመደገፍ ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡
ቋንቋው በዲግሪ ደረጃ መሰጠት መጀመሩንም ነው የቢሮ ኃላፊው የተናገሩት፡፡
ጉባዔው በስሩ የሚገኙ የባህል፣ ቅርስና ታሪክ ቋሚ ኮሚቴ እና የቋንቋና ትምህርት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢና አባላትን መርጧል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!