Fana: At a Speed of Life!

በ8 የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የሚከናወነው የመልሶ ግንባታ ሥራ በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በስምንት የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የሚከናወነው የመልሶ ግንባታ እና የአቅም ማሳደግ ሥራ በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገለጸ፡፡

በአገልግሎቱ የአዲስ አበባ ትራንስሚሽን፣ ዲስትሪቢዩሽን የመልሶ ግንባታና አቅም ማሳደግ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ አቶ ፍቅረሰላም ጌትነት እንደገለጹት÷በእነዚህ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የሚሰራው የዓቅም ማሳደግ ስራ የኤሌክትሪክ አገልግሎትን በአማካይ በ40 በመቶ ያሳድጋል፡፡

የአቃቂ 1 እና 2፣ አባ ሳሙኤል እና የጌጃ ነባር ማከፋፈያ ጣቢያዎች አቅም በአማካይ ከነባራቸው 7 ነጥብ 4 ወደ 13 ነጥብ 5 ሜጋ ቮልት አምፒር በመልሶ ግንባታው ከፍ እንደሚሉ ገልፀዋል፡፡

የሚገነቡት የጫንጮ የኃይል ማሰራጫ 7 ነጥብ 5፣ የጋፋት የመከላከያ እንጂነርንግ 15፣ ሁለት የቢሾፍቱ የኃይል ማከፋፈያዎች ደግሞ 7 ሜጋ ቮልት አምፒር አቅም እንዳላቸው ነው የጠቆሙት፡፡

የኃይል ማከፋፈያ መቆጣጣሪያ ቤቶች፣ የመንገድ ስራ፣ የኃይል ማስተላለፊያ እቃ ማስቀመጫ ግንባታ እና የተፋሰስ ሥራዎች 80 በመቶ የተጠናቀቁ ሲሆን÷ የፕሮጀክቶቹ የእቃ አቅርቦት 99 በመቶ መድረሱን ስራ አስኪያጁ አንስተዋል፡፡

የኃይል ማሰራጫ መግጠምና አገናኝ የኤሌክትሪክ መስመሮች ዝርጋታ ሥራም 40 በመቶ መጠናቀቁን ጠቁመዋል፡፡

የፕሮጀክቱ ወጪ 10 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር ያህሉ በአፍሪካ ልማት ባንክ እንዲሁም 65 ሚለየን ብር በኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደሚሸፍን ተገልጿል፡፡

ፕሮጀክቱ  ሐምሌ 2013 ዓ.ም የተጀመረ መሆኑን ያስታወሱት ሥራ አስኪያጁ÷ በ2015 ዓ.ም ጥቅምት ወር ላይ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የአዲስ አበባ ከተማና ዙሪያው የኃይል መቆራረጥ እና የብክነት ችግር እንደሚቀነስ እንዲሁም ያረጁ የኃይል ማከፋፈያዎችን ያሻሽላል ተብሎ እንደሚጠበቅ  መግለጻቸውንም ከአገልግሎቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.