Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ብቃት የሌላቸው አሽከርካሪዎች መንጃ ፍቃድ እንዳያገኙ የሚያደርግ አሰራር ሊተገበር ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ በብቃት ማነስ ምክንያት የሚከሰት የትራፊክ አደጋን ይቀንሳል የተባለ የአሽከርካሪ ብቃት መቆጣጠሪያ ስርአት ሊዘረጋ ነው።
 
የሚዘረጋው ስርአት ማንኛውም የአሽከርካሪነት ብቃት የሌለው ግለሰብ መንጃ ፍቃድ እንዳይወስድ የሚያደርግ መሆኑን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አሽከርካሪ ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን አስታውቋል።
 
በባለስልጣኑ የአሽከርካሪ ዘርፍ ምክትል ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሁላገርሽ ተፈራ የብቃት ማነስ ችግር እና ብቃት ለሌላቸው አሽከርካሪዎች መንጃ ፍቃድ ይሰጣል የሚል ጥቆማ በተደጋጋሚ ቢደርሳቸውም ተጨባጭ ማስረጃ ማግኘት አለመቻሉን ይናገራሉ።
 
ከዚህ ባለፈም በሙስና መንጃ ፈቃድ ይወጣል የሚል ቅሬታ እንደሚደርሳቸው ያነሱት ሃላፊዋ፥ ባለስልጣኑ እነዚህን ጥቆማዎች ታሳቢ በማድረግ ለሙስና ከፍት የሆኑ አሰራሮችን ለይቷል ብለዋል።
 
በዚህ መሰረት ፍቃድ ወስደው ስራ ላይ የሚገኙ 90 የመንጃ ፍቃድ ማሰልጠኛ ተቋማት ላይ በሚሰጡት የንድፈ ሃሳብና የተግባር ስልጠናዎች ላይ እንዲሁም በባለስልጣኑ የመንጃ ፍቃድ አሰራር ላይ የሚታዩ ለሙስና ተጋላጭ የሆኑ አሰራሮችን የመቅረፍ አሰራር እየተዘረጋ መሆኑን ገልፀዋል።
 
ከዚህ ባለፈም ሰልጣኞች ከንድፈ ሃሳብ ጀምሮ እስከ መፈተኛቸው ጊዜ ድረስ በትክክል መማራቸውን ለማረጋገጥ በአሻራቸው በየጊዜው ክትትል እንደሚደረግም አንስተዋል።
 
በዚህ መሰረት ማንኛውም የአሽከርካሪነት ብቃት የሌለው ሰልጣኝ መንጃ ፍቃድ መውሰድ እንዳይችል ይደረጋል ነው ያሉት።
 
አዲሱ የአሽከርካሪ ብቃት መቆጣጠሪያ ስርአት በአሁኑ ወቅት የሙከራ ስራ የጀመረ ሲሆን በተያዘው በጀት አመት ሙከራውን አጠናቆ ወደ ተግባር ይገባል ተብሏል።
 
ለዚሁ ስርአት አጋዥ የሆነ በካሜራ ተደገፈ ቁጥጥር የሚደረግበት የተግባር መፈተኛ ቦታ በከተማ አስተዳደሩ ይዘጋጃልም ነው የተባለው።
 
በተጨማሪም ባለስልጣኑ በፌደራል ብቻ ይሰጥ የነበረውን ብቁ የመንጃ ፍቃድ አሰልጣኝ የማፍራት አሰራርን በራሱ ለመጀመር መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
 
ይህም ብቁ አሽከርካሪ ከማፍራት በተጨማሪ ለሙስና ክፍት የሆኑ አሰራሮችን ይቀርፋል ተብሎ ታምኖበታል።
 
በታሪክ አዱኛ
 
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.