Fana: At a Speed of Life!

በክልሉ ባለሀብቶችን ለማበረታታት በመሰረተ ልማት የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው -አቶ አሻድሊ ሀሰን

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በማዕድን ዘርፍ ባለሀብቶችን ለማበረታታትና ተሳትፏቸውን ለማሰደግ በመሰረተ ልማት የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት ከፌደራል መንግስት ጋር ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አሻድሊ ሀሰን ገለጹ፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አሻድሊ ሀሰን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ የክልሉ መንግስት በማዕድን ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ዘርፉን ለባለሀብቶች ክፍት ማድረጉን ጠቁመው÷ በሚፈለገው ልክ በቂ ባለሀብቶች አለመገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
ባለሀብቶች ሲመጡ የእውቀት ሽግግር ለማድረግ ዝግጅት መደረጉን የገለጹት አቶ አሻድሊ÷ በመሰረተ ልማት የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት ከፌደራል መንግስት ጋር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኩርሙክ አካባቢ በወርቅ ማውጣት ሥራ የተሰማሩ ወገኖች በበኩላቸው÷ የባንክ፣ የኔትወርክ፣ የኤሌክትሪክ፣ እንዲሁም የመንገድ እና የውሃ ችግር ለወርቅ ማውጣት ስራው ፈተና እንደሆነባቸው ጠቁመው በአጠቃላይ የመሰረተ ልማት ችግር ውጤታማ እንዳንሆን አድርጎናል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ከወርቅ ማውጣት እስከ ማንጠር ድረስ ባለው ሂደት የሚጠቀሙባቸውን ኋላቀር አሰራሮች ለማዘመን ትብብር እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡
የክልሉ ማዕድን ልማት ዳይሬክተር ናስር ሙሀመድ በሰጡት ምላሽ÷ ችግሮቹ መኖራቸውን ገልጸው ይህም የተከሰተው ለበርካታ ዓመታት በበይ ተመልካችነት የቆዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በልዩ አነስተኛ ማኅበራት በማደራጀት ወደ ስራ እንዲገቡ በመደረጉና የፋይናንስ ችግር በመኖሩ ነው ብለዋል፡፡
በአፈወርቅ እያዩ
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.