በታንዛንያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 80 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ተመለሱ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በታንዛንያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 80 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ተሸኝተዋል፡፡
በዛሬው ዕለት በሶስተኛው ዙር በታንዛንያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያን ወደ አገራቸው ለመመለስ በተከናወነው ስራ 80 ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው መሸኘታቸው ተመላክቷል፡፡
የተቀሩትም በቀጣይ በተቀመጠላቸው የጉዞ ፕሮግራም መሠረት ወደ ኢትዮጵያ መመለስ እንዲችሉ አስፈላጊ የሆኑ ቅድመ ሁኔታዎች በመሟላት ላይ እንደሚገኙ በታንዛንያ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታለ፡፡
ታንዛንያን አቋርጦ ወደ ደቡብ አፍሪካ በሚደረግ ህገ-ወጥ ጉዞ በርካታ ኢትዮጵያውያን በታንዛኒያ መንግስት የፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር እየዋሉ ለእስር እንደሚዳረጉ ይታወቃል።
በርካታ ኢትዮጵያውያን በህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች በመታለል ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ከፍለው እጅግ አደገኛ የሆነ ህገ ወጥ ጉዞ የሚያደርጉ ሲሆን÷ በመንገዳቸው ላይ ለርሃብ፣ ለእስር፣ ለስቃይ ብሎም ለሞት እንደሚዳረጉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።