Fana: At a Speed of Life!

በጎንደር ከተማ ከሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 15 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጎንደር ከተማ ከሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን የከተማው ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ፍሰቱ በእጅጉ መጨመሩን የመምሪያው ኃላፊ አቶ ቻላቸው ዳኛቸው ገልጸዋል።

በውጪ ሀገር ጎብኚዎች ላይ ተወስኖ የቆየው የከተማው የቱሪዝም ዘርፍ በኮቪድ እና በሰላም እጦት ምክንያት ተቀዛቅዞ መቆየቱን አስታውሰው፥ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የሀገር ውስጥ ቱሪዝሙን ለማሳደግ በተደረገው ጥረት ውጤት መገኘቱን አስታውቀዋል።

በተለይም የገና እና የጥምቀት በዓላት ለቱሪዝሙ መነቃቃት አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ተናግረዋል።

“በተጨማሪም የአጼ ቴዎድሮስ ቁንዳላ ወደ ጎንደር ከተማ መጥቶ ለህዝብ እይታ ክፍት እንዲሆን መደረጉ እና የከተማውን የቱሪዝም ሀብት እና ጸጋዎች ለማስተዋወቅ የተደረገው ጥረት ሀገር ውስጥ የቱሪዝም ፍሰቱን አሳድጎታል” ነው ያሉት።

በ2013 በጀት ዓመት የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ቁጥር 57 ሺህ እንደነበር አስታውሰው፥ በ2014 በጀት ዓመት ይህ ቁጥር ወደ 325 ሺህ ማደጉን አስረድተዋል።

በአዲሱ በጀት ዓመት ለሀገር ውስጥ ቱሪዝም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ አመልክተው፥ የጎብኚዎችን ቁጥርም ወደ 700 ሺህ ለማድረስ ዕቅድ ተነድፎ ወደ ሥራ መግባቱን ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.