የሀገር ውስጥ ዜና

“መገናኛ ብዙኃን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ውጤታማ እንዲሆን ማኅበረሰቡን ከማንቃት ባለፈ ችግኝ መትከል ላይም የመሳተፍ ድርብ ሃላፊነት አለባቸው” – አቶ አድማሱ ዳምጠው

By Alemayehu Geremew

July 23, 2022

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የመገናኛ ብዙኃን ሚና የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ውጤታማ እንዲሆን ማኅበረሰቡን ከማንቃት ባለፈ፥ ችግኝ መትከል ላይም የመሳተፍ ድርብ ኃላፊነት እንዳለባቸው የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው ተናገሩ።

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አመራሮችና ሠራተኞች የአራተኛ ዙር አረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብርን ዛሬ ካራቆሬ በሚገኘው በኮርፖሬቱ የማሠራጫ ማዕከል ቅጥር ግቢ ውስጥ አከናውነዋል።

በችግች ተከላው ላይ የተሳተፉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው÷ አሁን ላይ ሀገሪቱ እያከናወነች ያለችው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የአየር ንብረት ለውጥ ለመቆጣጠር እና ሚዛኑን የጠበቀ የአየር ንብረት እንዲኖረን ለማድረግ ያስችላል ነው ያሉት፡፡

በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሩ ከተተከሉት ችግኞች ውስጥ ለምግብነት የሚውሉ ከመኖራቸውም ባሻገር፥ የሥራ ዕድልን በመፍጠር ረገድም ከፍተኛ ሚና አላቸው ብለዋል፡፡

ይህ የተሳካ እንዲሆን የመገናኛ ብዙኃን ሚና የጎላ መሆኑን የተናገሩት አቶ አድማሱ፥ በተለይም ፋና እንደ መርሁ “በሕይወት ፍጥነት” በዘርፉ የተሠሩ ሥራዎችን ከመዘገብ ባለፈ ከመደበኛ ሥራው ጎን ለጎን በሀገራዊ ሥራዎች ላይ በንቃት እየተሳተፈ እንደሚገኝም ነው የገለጹት፡፡

በዚህም መሰረት የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩን ሀገራዊ ጉዳይና ለትውልድ የሚሻገር መሆኑን ለኅብረተሰቡ በማስገንዘብ ረገድ የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

“ችግኝ መትከል ብቻውን ለውጥ አያመጣም” ያሉት አቶ አድማሱ፥ የሚተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁ ለእንክብካቤውም ሥርዓት ተበጅቶለታል ብለዋል።

ከዚህ ቀደም የተተከሉት ለምግብነት የሚውሉና ሌሎች የችግኝ ዓይነቶች ሲሆኑ፥ በዛሬው ዕለትም የአካባቢውን የአየር ንብረትና ሥነ-ምኅዳር የሚያስጠብቁ ችግኞች መተከላቸውን ነው የጠቆሙት።

በሃይማኖት ኢያሱ

ፎቶ ÷ በዳንዔል ሙሉ