Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል ለተለያዩ ማዕድናት ልማት የሚሆኑ በርካታ አካባቢዎች በጥናት ተለይተዋል – ዶክተር ይልቃል ከፋለ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ለተለያዩ ማዕድናት ልማት የሚሆኑ በርካታ አካባቢዎች በጥናት መለየታቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ተናገሩ።

ርዕሰ መስተዳድሩ የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ለምክር ቤቱ ያቀረቡ ሲሆን፥ በሪፖርታቸውም በክልሉ የሚገኘውን የማዕድን ሐብት በመለየት የተለያዩ ቦታዎችን ለኢንቨስትመንት ምቹ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ዶክተር ይልቃል ከፋለ፥ ባሳለፍነው ዓመት ብቻ በሰሜን ወሎ ግዳን ወረዳ ለመጠጥ ውሃ ማጣሪያነት የሚያገለግል የ10 ካሬ ኪሎ ሜትር የ”ናይትሮላይት ዚኦላይት” ማዕድን ፍለጋ እና የክምችት ጥናት እንዲሁም በአዊ ዞን በዚገም ወረዳ ደግሞ ለሴራሚክ እና መስታወት መሥሪያነት የሚያገለግል በ26 ነጥብ 66 ካሬ ኪሎ ሜትር ላይ የተካሄደ የ”ቤንቶናይት” ማዕድን ክምችት ፍለጋ ተጠናቆ ለሚመለከታቸው ዞኖች ተልኳል ብለዋል።

በሰሜን ሸዋ እና በአዊ ዞን እንዲሁም በጃዊ እና ቋራ አካባቢዎች የእምነበረድ፣ ግራናይት፣ ሲሊካሳንድ ወርቅ እና የወርቅ አለት ማዕድናት ከፍ ባለ መጠን መገኘታቸውንም ጭምር ነው ርዕሰ መስተዳድሩ በሪፖርታቸው ያመላከቱት።

በተመሳሳይ በደቡብ ወሎ ዞን ቦረና ወረዳ ፣ በምሥራቅ ጎጃም ዞን እነብሴ ሳርምድር እና እናርጅ እና እናውጋ ወረዳዎች በ1 ሺህ 8 ካሬ ኪሎ ሜትር ዙሪያ የብረት፣ የላይምስቶን፣ የጅፕሰም ፣ የኒኬል እና የጌጣጌጥ ማዕድናት በብዛት መኖሩ ተረጋግጧል።

በእነዚህ አካባቢዎች የተገኙት ማዕድናት ለሰፋፊ የብረት እና የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ግብዓት ስለሚሆኑ ኢንዱስትሪዎቹን ለማቋቋም እንደሚያስችል ተናግረዋል።

በክልልሉ የድንጋይ ከሰል ክምችት ለመለየት በተደረገ ጥናት እስካሁን ድረስ በውጫሌ፣ በጭልጋ፣ በደንቢያ፣ በደብረ ኤሊያስ፣ በተንታ መቅደላ እና በአንኮበር ወረዳዎች ማዕድኑ እንዳለ ማረጋገጥ ተችሏል።

የማዕድን ፈቃድ ለመስጠት በተሰራው ሥራም 57 የብቃት ማረጋገጫ እንዲሁም 2 ቢሊየን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 38 ባለሐብቶች ፈቃድ ተሰጥቷል።

በከፍተኛ ደረጃ የኢንዱስትሪ እና የግንባታ ማዕድናትን ለማምረት 3 ቢሊየን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 12 ድርጅቶችም ፈቃድ መሠጠቱ ነው የተገለጸው።

በቀጣይም ለማዕድን ልማት ኢንቨስትመንት ዘርፉ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት የውጭ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የመተካት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡

በምንይችል አዘዘው

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.