በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እስካሁን ከ5 ቢሊየን በላይ ችግኞች ተተክለዋል
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እስካሁን ከ5 ቢሊየን በላይ ችግኞች መተከላቸውን የብሔራዊ አረንጓዴ አሻራ መርሐግብር የቴክኒክ ኮሚቴ ገለጸ።
በኢትዮጵያ ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ በሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር “አሻራችን ለልጆቻችን” በሚል መሪ ሀሳብ 6 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል እቅድ ተይዞ እየተከናወነ ይገኛል።
የብሔራዊ አረንጓዴ አሻራ መርሐግብር የቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ ዶክተር አደፍርስ ወርቁ ÷የእስካሁኑ ሂደት ስኬታማ መሆኑን ገልጸው በዘንድሮው መርሐግብር በተለይም ለአገር በቀል እጽዋቶች እንዲሁም ለደን ልማት የሚውሉ ዝርያዎች ትኩረት በመስጠት በመተከል ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
እንዲሁም ከሚተከሉ ችግኞች 52 በመቶው ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬና የቅመማ ቅመም ዝርያዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ለመትከል ከታቀደው 6 ቢሊየን ችግኝ እስካሁን 5 ቢሊየን ችግኝ መተከሉንም ዶክተር አደፍርስ ተናግረዋል።
የእቅዱን ግብ ለማሳካት እስከ ሐምሌ መጨረሻ ድረስ የችግኝ ተከላው እንደሚቀጥል አረጋግጠው የመጽደቅ መጠኑ ከፍ እንዲልም እንክብካቤው ቀጣይነት ይኖረዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ኢትዮጵያ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በተከታታይ አራት ዓመታት 20 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ግብ ይዛ እየሠራች መሆኑ ይታወቃል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!