Fana: At a Speed of Life!

የተቀናጀ የመንገድ ትራፊክ ቁጥጥር እና የግንዛቤ ፈጠራ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሀገሪቱ የሚስተዋለውን የትራፊክ አደጋ ለመቆጣጠር የግንዛቤ ፈጠራና የተቀናጀ የመንገድ ትራፊክ ቁጥጥር ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል።

የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ያደታ በዛሬው ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፥ የተሽከርካሪዎች ቁጥር አሁን ላይ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ እንደሚገኝ አንስተዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም የመንገድ ትራፊክ ቁጥጥር በማድረግ በአግባቡ አገልግሎት እንዲሠጥ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

የመንገድ ትራፊክ አደጋው በ2011 እና 2012 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ቢቀንስም ከ10 ሺህ ተሽከርካሪ 27 ለማድረስ ብዙ መስራት እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።

አሁን ለሚታየው የመንገድ ትራፊክ አደጋ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት የመንገድ ደህንነት ትምህርት በመደበኛ ትምህርት እና በጎልማሶች ትምህርት እንዲካተት በማድረግ እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል።

ለዚህም ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የመንጃ ፈቃድ፣ የተሽከርካሪ ምርመራ እና የትራፊክ ቁጥጥር ስርዓቱን ለማዘመን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ስራ መጀመሩን ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ህብረተሰቡም የትራፊክ አደጋን አስከፊነት በመገንዘብ ለቁጥጥር ስራው ተባባሪነቱ እየጎለበተ በመምጣቱ የግንዛቤ ፈጠራው እና የቁጥጥር ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.