Fana: At a Speed of Life!

አይ ኤም ኤፍ የዓለም ኢኮኖሚ እድገት ትንበያን ወደ 3.2 በመቶ ዝቅ አደረገ

 

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) ትናንት በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚያዊ እድገት ዙሪያ ያለውን ትንበያ ወደ 3.2 በመቶ ዝቅ አድርጓል፡፡

ዓለም ከፍተኛ የዋጋ ግሽበትን ጨምሮ አሁንም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና በዩክሬን ግጭት እየተንገዳገደች ያለችበት ሁኔታ ከፍ ያለ ውጥረት ውስጥ መግባቷንመሰረት በማድረግ ነው አይ ኤም ኤፍ ትንበያውን ዝቅ ያደረገው።

ተቋሙ ትንበያውን በሚያዝያ 2022 ካወጣው የዓለም ኢኮኖሚ ዕይታ አንፃር በ0.4 በመቶ ዝቅ ማድረጉ ነው የተጠቀሰው፡፡

ተቋሙ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮች ዓለምን ከአቅም በላይ በሆነ መልኩ ወደ ቀውስ ለማስገባት እያንገዳገዷት ይገኛሉ ነው ያለው።

የምልከታ ዘገባው በሦስቱ የዓለም ታላላቅ ኢኮኖሚያዊ አቅም ባላቸው ሀገራት ማለትም በአሜሪካ፣ በቻይና እና በአውሮፓ አካባቢ ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ እያሳደረ ያለ ዕውነታ መኖሩንም አመላክቷል።

የአሜሪካ እና ዋና ዋና የአውሮፓ ሀገራት ከተጠበቀው በላይ ከፍ ያለ የዋጋ ንረት እያጋጠማቸው መሆኑን የጠቆመው የአይ ኤም ኤፍ ትንበያ፥ ይህ ደግሞ በዓለም ዙሪያ የፋይናንስ እንቅስቃሴን አጣብቂኝ ውስጥ እየከተተ ነው ሲል  አመላክቷል።

ቻይና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና የፋይናነስ ተቋማት ሀብት እንቅስቀሴ መቀዛቀዝ ምክንያት ጫና ውስጥ ወድቃለች ሲልም የትንበያ ሪፖርቱ አስፍሯል።

የጂኦ-ፖለቲካው መከፋፈል የዓለም ንግድ እና ትብብርን የበለጠ ሊያደናቅፍ ይችላል በማለት ሪፖርቱ ያመላከተ ሲሆን፥ የሩስያ እና የዩክሬን ግጭት በአውሮፓ የኃይል አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ጫና በመፍጠሩ በርካታ አሉታዊ ውጤቶች እያመጣ እንደሆነም ገልጿል።

አይ ኤም ኤፍ በ2022 ላደጉ ሀገራት የ2.5 በመቶ የኢኮኖሚ  እድገት እንደሚኖር ሲተነብይ፥ ለታዳጊ ሀገራት ደግሞ የ3.6 በመቶ ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ነው የተነበየው።

የምግብ እና የኃይል ዋጋ መናር እንዲሁም የአቅርቦትና ፍላጎት አለመመጣጠን የዓለም የዋጋ ግሽበት እንዲያንሰራራ አድርጎታልም ብሏል።

ዓለም አቀፍ የዋጋ ጭማሪን ተከትሎ የኑሮ ደረጃ እያሽቆለቆለ በመጣ ቁጥር የዋጋ ንረትን መቆጣጠር ለፖሊሲ አውጪዎች ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል ሲልም አይኤምኤፍ ማስጠንቀቁን ሲጂቲኤን ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.