Fana: At a Speed of Life!

የመረጃ መንታፊዎችን ለመከላከል የሳይበር ደኅንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀረፃ ላይ በተቋማት መካከል ትብብር እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሁዋዌ ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን የሦስት ቀናት የሳይበር ደኅንነት ሥልጠና መሥጠቱን አስታወቀ።

ሁዋዌ ሲሰጥ የቆየውን የሳይበር ደኅንነት ሥልጠና የመሩት ከፍተኛ የሳይበር ደኅንነት ባለሙያዎቹ መሆናቸውም ነው የተጠቆመው።

የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ባልቻ ሬባ በሥልጠናው የመክፈቻ መርሐ-ግብር ላይ የተገኙ ሲሆን፥ በንግግራቸው ሁዋዌይ “ዲጂታል ኢትዮጵያን” ለመገንባት እያደረገ ላለው ጥረት ዕውቅና በመስጠት ማድነቃቸው ተመላክቷል፡፡

ኢንጂነር ባልቻ፥ የሳይበር ደኅንነት ጉዳይ ከሌላ አካል የሚቀርብልን ነገር ሳይሆን እኛው እስትራቴጂ በመቅረጽ በውስጥ የምንገነባው ሥርዓት ነው” ማለታቸውም ተገልጿል።

በሳይበር ቴክኖሎጂ የሚሰሩ አካላት፣ የንግድ ተቋማት ፣ ኩባንያዎች ፣ ኢንዱስትሪዎች እና መሪዎች ሁሉ ሥርዓቶቻቸው የመረጃ መንታፊዎች ሰለባ እንዳይሆኑ የሳይበር ደኅንነት ፖሊሲ እና ስትራቴጂ በመቅረጽ በትብብር እና በተጠያቂነት መሥራት እንዳለባቸውም ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡

የሁዋዌ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቼን ሚንግሊያንግ ÷ የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን በኢትዮጵያ የተሻለ የቴክኖሎጂ ትሥሥር ለመገንባት እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከሀገራቸው ጋር በመተባበር የ5ኛውን ትውልድ ቴክኖሎጂ “5ጂ” ዕውን ለማድረግ ላደረገችው ጥረትም ያላቸውን አክብሮት ገልጸዋል።

ዓለማችን በበይነ-መረብ አንድ መንደር እየሆነች መምጣቷንና በቴክኖሎጂም ከምን ጊዜውም በላይ መተሳሰሯን ሥራ አስፈጻሚው ገልጸው የመንግስትና የግል ተቋማት በሚያደርጓቸው የበይነ-መረብ እና የቴክኖሎጂ ግንኙነቶች ሁሉ ሥርዓቶቻቸውን ለመጠበቅ የሳይበር ደኅንነት እና ግላዊነት ጥበቃ መተግበር ከጊዜ ወደ ጊዜ እጅግ አስፈላጊ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

ሥልጠናው በዓለም አቀፍ የሳይበር ደኅንነት ተግዳሮቶች እና ትንታኔዎች ፣ በሳይበር ደኅንነት አስተዳደር ፣ በ”5ጂ” ደኅንነት እና ቴክኖሎጂዎች እንዲሁም ሁዋዌ የሳይበር ደኅንነት ሥርዓት በመዘርጋት የሚሰጣቸውን የደኅንነት ማረጋገጫ አገልግሎቶች መሸፈኑም ነው የተነገረው፡፡

ሁዋዌ በዓለምአቀፍ ደረጃ 7 የሳይበር ደኅንነት ላይ የሚሰሩ ማዕከላት አቋቁሞ እየሰራ ይገኛል፡፡

በዘርፉ ሙሉ ጊዜ ሰጥተው ጥናትና ምርምር የሚሠሩ 3 ሺህ ያህል ሠራተኞችም እንዳሉት ከሁዋዌ ኢትዮጵያ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.