Fana: At a Speed of Life!

አትሌቶቻችን ያስመዘገቡት ድል የኢትዮጵያውያንን አንድነት ለዓለም በተምሳሌትነት ያሳየ ነው ÷አቶ አሻድሊ ሀሰን

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አትሌቶቻችን ያስመዘገቡት ድል የኢትዮጵያውያንን አንድነት ለዓለም በተምሳሌትነት ያሳየ ነው ሲሉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ገለጹ፡፡
ርዕሰ-መስተዳድሩ በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ላስመዘገቡት አንጸባራቂ ድል አድናቆታቸውን ገልፀዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ያስመዘገቡት ድል ፈተናን የመሻገሪያው ምስጢር አንድነት መሆኑን እና ከራስ አልፎ ለሀገር ክብር በአንድነት መቆምን በተግባር ያረጋገጠ ነው ብለዋል፡፡
ፈተናዎቻችን ከውስጥና ከውጪ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን መልካቸውን እየቀያየሩ መፈጠራቸው፣ አንድነታችንን ለማይፈልጉ ኃይሎች የማንሻገራቸው መስሏቸው ነበር ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ ኢትዮጵያ በታሪካዊ ጀግንነት የቆየች እና አሁንም ብዙ ጀግኖች ያሏት ሀገር ናት ሲሉ አውስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለሀገራቸው መስዋዕትነት የሚከፍሉ ውድ ልጆች ያሏት ሀገር መሆኗን ገልጸው÷ እኛን አጥፍተው እነሱ ከፍ ሊሉ ደጋግመው የሻቱ ጠላቶቻችን ዛሬ አንገታቸውን ባስደፋናቸው ልክ ነገም ቀና እንዳይሉ ለማድረግ በጋራ መቆም አለብን ብለዋል፡፡
አቶ አሻድሊ የአትሌቶቻችን የድል አድራጊነት ሚስጥር ከራስ አልፎ በአንድነት ለሀገር ማሰብ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በክልሉ ለአትሌቶቹ ደማቅ የምስጋና መርሐ-ግብር በነገው ዕለት እንደሚካሄድ ጠቁመው ÷ የክልሉ ሕዝብም አትሌቶቹን እንዲያመሰግን ጥሪ አቅረበዋል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.