Fana: At a Speed of Life!

አዋሽ ባንክ እና 9 የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የ 5 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር የብድር ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የ 5 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር የብድር ስምምነት ተፈረመ።

የብድር ስምምነቱ በአዋሽ ባንክ እና በዘጠኝ ማይክሮ የፋይናንስ ተቋማት መካከል ተፈጽሟል፡፡

በፊርማ ሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የሥራና ክኅሎት ሚኒስትር ክብርት ሙፈሪሃት ካሚል አዋሽ ባንክ መንግስት ያስቀመጠውን የፖሊሲ ሀሳብ በመተግበር ደረጃ ግንባር ቀደም በመሆኑ አመስግነዋል።

ይህ መልካም ተግባር ሚሊየን ዜጎቻችንን የዘነጋ አካሄድ እንዳይፈጠር በተስተካከለ መሰረት ላይ የሚገነባ ኢኮኖሚ እንዲኖረን የሚያደርግ ጥሩ ጅምሮ ነውም ብለዋል፡፡

የብድር ስምምነቱ ከ300ሺህ በላይ ወጣቶችን እና በስራቸው የሚገኙ ቤተሰቦቻቸውን ተጠቃሚ የሚያደርግ ዕድል በመሆኑ ተበዳሪዎቹ ለታለመለት ዓላማ እንዲያውሉት አደራ ብለዋል ወይዘሮ ሙፈሪሃት።

ወጣቶችን በክኅሎት አብቅተን በዕውቀት ደግፈን እና አዘጋጅተን በፋይናንስ ስንደግፍ ውጤታማ ስለምንሆን ሌሎች ባንኮችም ይህን መከተል አለባቸው ብለዋል፡፡

ሚኒስትሯ ÷ በየደረጃው ያሉ ወጣቶቻችንንም ለሥራ ብቁ ለማድረግ ማነቆ የሆኑ የሥርዓተ-ሥልጠና እና የፋይናንስ ችግሮችን ለመፍታት ከግሉ ዘርፍ እና አጋር አካላት ጋር ትብብራችንን አጠናክረን ቀጥለናል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የአዋሽ ባንክ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፀሐይ ሽፈራው ÷ ባንኩ ከ2016 ጀምሮ ለጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የተለያዩ የብድር አቅርቦቶችን ማድረጉን በማስታወስ በቅርቡ ይፋ ባደረገው “ታታሪዎቹ” የተሰኘ የወጣት ሥራ ፈጣሪዎችን የሚያበረታታ ውድድርም 8ሺህ አመልካቾችን ተቀብሎ እያወዳደረ መሆኑን ጠቅሰው ይህም ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት ያሳያል ብለዋል፡፡

ስምምነቱን የተፈራረሙትን ዘጠኝ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትን በመወከል ስሜታቸውን የገለፁት ኃላፊዎች የተፈቀደው ብድር ኢንተር ፕራይዞችን እና ወጣቶችን የማሳደግ ሚናው ትልቅ በመሆኑ አዋሽ ባንክን አመስግነዋል፡፡

ፈርስት ኮንሰልት ባቀረበው ማብራሪያ የ5.5 ቢሊየን ብር ብድሩ 110 ሺህ ኢንተርፕራይዞችን ተደራሽ የሚያደርግ ሲሆን በዚህም እስከ 330 ሺህ ወጣቶች እና ቤተሰቦቻቸው ተጠቃሚ የሆናሉ ተብሏል፡፡

ማይክሮ ፋይናንስ እና ባንኩን በማስተሳሰር ትልቅ ሚና የተጫወቱትን ማስተርካርድ ፋውንዴሽን እና ፈርስት ኮንሰልት ብሪጅ መሆናቸውን ከሥራና ክኅሎት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.