የጎንደር ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች በመጠጥ ውሃ ችግር ላይ እንደሚገኙ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ እና የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢ/ር ሃብታሙ ኢተፋ በጎንደር ከተማ እያደረጉ ባለው ጉብኝት የከተማዋ ነዋሪዎች በከፍተኛ በመጠጥ ውሃ ችግር ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡
ጎንደር ከተማ በየቀኑ 70ሺህ ሜትር ኪዮብ ውሃ ብትፈልግም ለከተማዋ በአሁኑ ስዓት እየቀረበ የሚገኘው ግን 13 ሺህ ሜትር ኪዮብ ውሃ ብቻ መሆኑ ነዋሪዎቿን ለማህበራዊ ችግሮች ማጋለጡ ተገልጿል፡፡
በከተማዋ ያለው የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግርም ከተማዋ የምትታወቅበት የቱሪዝም እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያደረሰ እንደሚገኝም ነው የተጠቆመው።
የከተማ አስተዳደሩ ችግሩን ለመቅረፍ የአጭር ጊዜ እቅድ አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን ፥ ከከተማ አስተዳደሩ ጥረት በተጨማሪ የክልሉና የፌዴራል መንግስት ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት የሚያግዝ ውይይት ዛሬ በጎንደር ከተማ ይካሄዳል ተብሏል።
በውይይቱ ላይ ለመሳተፍ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ፣ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ፣ የአማራ ብልጽግና ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ግርማ የሽጥላን ጨምሮ ሚኒስትር ዴኤታዎች ፣ አምባሳደሮች እንዲሁም የክልል ቢሮ ሃላፊዎች ጎንደር ከተማ ተገኝተዋል።
የውሃና ኢነርጅ ሚኒስትርና የተቋማቸው ሰራተኞች የልዑካን ቡድን በጎንደር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አከናነዋል ፤ በግንባታ ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶችንም ጎብኝተዋል።
በዚህም ለ20 ዓመታት የንፁህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረውን የአንገረብ ግድብ የጎበኙ ሲሆን ፥ ግድቡ በአሁኑ ሰዓት በደለል በመሞላቱ የአገልግሎት ጊዜውን እየጨረሰ መሆኑ ተነግሯል።
የጎንደር ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ላለፉት አምስት ዓመታት በመጠጥ ውሃ ችግር ላይ እንደሚገኙም በጉብኘቱ ወቅት ተነስቷል።
ለንፁህ መጠጥ ውሃና ለመስኖ አገልግሎት ተብሎ ላለፉት 13 ዓመታት ግንባታው የተጓተተውን የመገጭ የውሃ መስኖ ፕሮጀክትን የልዑካን ቡድኑ የጎበኘ ሲሆን ፥ ከሁለት ዓመታት በፊት ከ500 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበት የአገልግሎት መስተጓጉል የደረሰበትን የቆላድባ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክትንም ተመልክቷል።
የልዑካን ቡድኑ በከተማዋ በሚኖረው ቆይታ በችግኝ ተከላ መርሐ ግብር የተሳተፈ ሲሆን ፥ ከበጎ ፈቃድ የክረምት አገልግሎት መካከል የአቅመ ደካሞችን ቤት በመገንባት እንደሚሳተፍም ተገልጿል።
በበላይነህ ዘለዓለም እና ምንይችል አዘዘው
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!