Fana: At a Speed of Life!

ሰርጎ ለመግባት የሞከረው አልሸባብ የሽብር ቡድን ዳግም ከፍተኛ ኪሳራ ተከናንቦ ወደ መጣበት ተመልሷል – ሜጀር ጀኔራል ተስፋዬ አያሌው

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ወደ ኢትዮጵያ ሰርጎ ለመግባት የሞከረው የአልሸባብ የሽብር ቡድን በጸጥታ ኃይሉ በተወሰደበት እርምጃ ዳግም ከፍተኛ ኪሳራ ተከናንቦ ወደ መጣበት መመለሱን የመከላከያ ኃይል ስምሪት ኃላፊና ጊዜያዊ የፀጥታ ኮማንድ ፖስት አስተባባሪ ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው ተናገሩ።

ሜጀር ጀኔራል ተስፋዬ ለኢዜአ እንደተናገሩት ባለፉት ቀናት ከኢፌዴሪ አየር ኃይል ጋር በመቀናጀት በተወሰደው እርምጃ የሽብር ቡድኑ ኢትዮጵያን ለማጥቃት ያዘጋጃቸውን የትጥቅና ስንቅ ዴፖዎች ማውደም ተችሏል፡፡

ነገር ግን የሽብር ቡድኑ ዛሬ ሌሊት ላይ የተበታተነ ኃይሉን በማሰባሰብ ኢትዮጵያና ሶማሊያ በሚዋሰኑበት አካባቢ ወደ ሀገር ውስጥ ሰርጎ በመግባት ጥቃት ለመፈጸም መሞከሩንም ሜጀር ጀኔራሉ ተናግረዋል፡፡

ሆኖም የጸጥታ ኃይሉ በወሰደው እርምጃ የሽብር ቡድኑ ዳግም ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራዎችን ተከናንቦ ወደ መጣበት መመለሱን አብራርተዋል።

እስካሁን ባለው መረጃም ከ150 በላይ የሽብር ቡድኑ አባላት መደምሰሳቸውንና የሽብር ቡድኑ ለአጥፍቶ መጥፋት ያዘጋጃቸው ተሽከርካሪዎች መውደማቸውን እና የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች እንደተማረኩ ገልፀዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የመከላከያ ሰራዊትና ጥምር የፀጥታ ኃይሉ የሽብር ቡድኑን ትንኮሳዎች ለመመከት በሙሉ ቁመና ላይ መሆኑን የጠቀሱት ሜጀር ጀኔራል ተስፋዬ፥ የሶማሌ ክልል ህዝብ ለመከላከያ ሰራዊቱና ለክልሉ ልዩ ኃይል ያለውን ደጀንነት በተግባር እያሳየ መሆኑን ጠቁመዋል።
የመከላከያ ሰራዊትና የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይልን ጨምሮ የፀጥታ ኮማንድ ፖስቱ በአካባቢው የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ለመድፈር በሚሞክር የትኛውም ኃይል ላይ እርምጃ ለመውሰድ በተጠንቀቅ ላይ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.