ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ከኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ከኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር በናይሮቢ ተገናኝተው ተወያይተዋል።
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የስራ ጉብኝት ለማድረግ በዛሬው እለት ኬንያ ናይሮቢ ገብተዋል።
በቆይታቸውም ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ከኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር በናይሮቢ ብሄራዊ ቤተ መንግስት ተገናኝተው ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም በሁለትዮሽ እና ባለብዙ ዘፍር ጉዳዮች ላይ የመከሩ ሲሆን፥ በሁለቱ ሀገራት አዋሳኝ ላይ የሚኖሩ ማህበረሰቦችን ሰላም ማስጠበቅ እና በምስራቅ አፍሪካ በተከሰተው የረሃ አንበጣ ወረርሽኝ ዙሪያ ተወያይተዋል።
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ እና ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ አክለውም በአባይ ተፋሰስ ዙሪያ እየተስተዋሉ ባሉ ችግሮች ዙሪያም ምክክር አድርገዋል።
በዚሁ ወቅትም ፕሬዚዳንት ሳህለወረቅ ዘውዴ ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ለፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ገለፃ አድርገዋል።
በተጨማሪም በግድቡ ዙሪያ በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ መካከል እየተደረገ ስላለው ድርድር ማብራሪያ የሰጡት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፥ ኢትዮጵያ ከአባይ ተፋሰስ ሀገራት ጋር የሁሉንም ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ የምትሰራውን ስራ አጠናክራ እንደምትቀጥልም አስታውቅዋል።
ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ አፍሪካ በየጊዜ እየጨመረ የመጣውን የህዝብ ፍላጎት ለማሟላት ተፈጥሯዊ ሀብቷን ዘላቂነት ባለው መልኩ መጠቀም ይገባታል ብለዋል።
በዚህ ላይ ፕሬዚዳንቱ የተፈጥሮ ሀብትን ፍትሃዊ እና መክንያታዊ በሆነ መንገድ መጠቀም እንደሚገባም አስምረውበታል።
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ እና ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በውይይታቸውም ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መንፈስ ያላቸው መፍትሄዎች እንደሚያስፈልጉ ገልፀው፤ ሀገራት ሁሉንም እኩል ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ የአፍሪካ ህብረት አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርግ ይገባልም ብለዋል።
በተጨማሪም በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በተከሰተው እና አሁን ላይ ስጋት እየሆነ ባለው የበረሃ አንበጣ መንጋ ወረርሽኝ ዙሪያም የተወያዩ ሲሆን፥ በሁለቱ ሀገራት ብሎም በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ስጋት እየፈጠረ ያለውን የበረሃ አንበጣ ለመከላከል በጋራ እንዲሁም በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) በኩል እንደሚሰሩም ገልፀዋል።
በውይይት ወቅትም ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በኬንያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እንዲያደርጉ በፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ግብዣ የቀረበላቸው ሲሆን፥ ፕሬዚዳንቷም ግብዣውን መቀበላቸውን ገልፀዋል።