Fana: At a Speed of Life!

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከ67 ሺህ በላይ ወጣቶች የሚሳተፉበት የክረምት የበጎ የፈቃድ አገልግሎት ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል “በጎነት ለኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል ከ67 ሺህ 800 በላይ ወጣቶች የሚሳተፉበት የ2014 የወጣቶች የክረምት የበጎ የፈቃድ አገልግሎት ዛሬ በይፋ ተጀምሯል፡፡
የክልሉ የሴቶች ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ የወጣቶች ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ አቢ ጀጎራ በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ በያዝነው የክረምት ወቅት ከ67 ሺህ 800 በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ይሳተፋሉ ብለዋል፡፡
ወጣቶች በበጋና በክረምት ወራት በርካታ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችን እያከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኙት አቶ በድሉ አዱኛ በበኩላቸው÷ በክረምት የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት በተለያዩ መስኮች 40 ሚሊየን የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡
ከ11 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለማከናወን ዕቅድ መያዙን ጠቁመው÷ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሐ ግብሩ እስከ መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም እንደሚቀጥል አብራርተዋል፡፡
በክረምቱ የበጎ ፈቃድ ወቅት÷ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር አካል የሆነ ችግኝ ተከላ፣ የአቅመ ደካሞች ቤት እድሳት፣ ሰላምና ደኅንነትን ማጠናከር፣ ደም ልገሳ እና ሌሎችም ሰብዓዊ ተግባራት ይከናወናሉ መባሉን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.