ኢትዮጵያ በእስልምና ታሪክ ውስጥ ያላትን ቦታ በተገቢው መልኩ ለዓለም ማስተዋወቅ እንደሚገባ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በእስልምና ታሪክ ውስጥ ያላትን ቦታ በተገቢው መልኩ በማስተዋወቅ ዳያስፖራዎች የሀገርን በጎ ገፅታ መገንባት እንዳለባቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ እና የኢድ እስከ ኢድ ብሔራዊ ኮሚቴ ጣምራ ሰብሳቢ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ተናገሩ።
በኢድ እስከ ኢድ ብሔራዊ ኮሚቴ አዘጋጅነት የተዘጋጀው እና ኢትዮጵያ ለእስልምና እምነት እና እድገት ያበረከተችውን አስተዋፅዖ ለዓለም ይበልጥ ማስተዋወቅ በሚቻልባቸው ሁኔታ ላይ ያተኮረ ምክክር በጂማ ተካሂዷል፡፡
አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በውይይቱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ኢትዮጵያ ለእስልምና እምነት እድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያላቸው ሀብቶችን የያዘች ሀገር መሆኗን ጠቁመዋል።
እነዚህን ሀብቶች በሚገባ በመያዝ ለዓለም አስተዋውቆ የሀገርን ገፅታ በበጎ መገንባት ያስፈልጋልም ብለዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼክ ሀጂ ቱፋ ኢብራሂም በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ በቅዱስ ቁርዓን ያላት መልካም ስም ታላቅ ቢሆንም ይህንን በሚገባ ማስተዋወቅ አለመቻሉን አውስተዋል።
በእስልምና ታሪክ ውስጥ ኢትዮጵያ ያላትን ስም በመላ ዓለም ያለ የዳያስፖራ ማህበረሰብ በሚገባ ተረድቶ ታሪኩን እንዲያስተዋውቅም ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እንድሪስ እንደገለጹት÷ የዳያስፖራው ማህበረሰብ ወደ ሀገር ቤት እንዲመጣ ጥሪ የቀረበበት ዋነኛ ምክንያት ዳያስፖራዎች ሀገሪቱ ያላትን ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊ እና ባህላዊ እሴቶች ይበልጥ አውቀው ለዓለም እንዲያስተዋውቁ ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ከኢትዮጵያ ባሻገር በመከከላኛው ምስራቅ እና በሌሎች ሀገራት ያሳረፏቸው ደማቅ ዐሻራዎች መኖራቸውን ጠቁመው÷ ይህን ሀብት ለሀገር በሚጠቅም መልኩ እንዲጠበቅና እንዲተዋወቅ ከዳያስፖራው ጋር በጥብቅ መስራት ያስፈልጋል ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!