በኒውዮርክ እየተባባሰ የመጣውን የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝ ለመግታት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታወጀ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኒውዮርክ ገዥ ካቲ ሆቹል የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመግታት የሚያስችሉ እርምጃዎችን ለመውሰድ በግዛቷ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጃቸውን አስታወቁ።
የአሜሪካው የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል ÷ ከትናንትና ጀምሮ በኒውዮርክ ግዛት በዝንጀሮ ፈንጣጣ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ እንደመጣና በአሁኑ ጊዜም 1 ሺህ 345 ያህል ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው እንደተረጋገጠ በሪፖርቱ አመላክቷል፡፡
ገዢዋ በኒውዮርክ የቫይረሱ የሥርጭት መጠን ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቅሰው ለመቆጣጠርም አስተዳደራቸው አስፈላጊውን ሁሉ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቀዋል፡፡
በኒውዮርክ በርከት ያሉ የክትባት መድሃኒቶችን ለማግኘትና የልየታ ምርመራዎችንም ለማስፋት እየተሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት።
የግዛቷ ነዋሪዎች ከወረርሽኙ መጠበቅ የሚችሉበትን መንገድ በማስተማር ላይ ንእንደሚገኙ ነው የጠቆሙት፡፡
አሁን ላይ ለግዛቷ ነዋሪዎች ተጨማሪ 110 ሺህ የዝንጀሮ ፈንጣጣ መከላከያ ክትባት የተገኘ ሲሆን እስካሁን የተገኘውን አጠቃላይ የክትባት መድሃኒት ቁጥር 170 ሺህ ዶዝ እንደሚያደርሰውም አር ቲ ዘግቧል፡፡
በሌላ በኩል በካሊፎርኒያ 799 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውም ነው የተነገረው።
የዓለም ጤና ድርጅት ከቀናት በፊት የዝንጅሮ ፈንጣጣን አሳሳቢ በሽታ ነው ማለቱ ይታወሳል።